ኮምፖስት አዘጋጅቶ መጠቀም የሰብል ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አንፃር ያለው አስተዋፅኦ በጣም የተሻለ ነው።
ለዚህም ከብዙ በጥቂቱ ለመግለፅ።
*
1/ኮምፖስት በሰብሎች የዕድገት ጊዜያት በሙሉ አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን አሟልቶ ያቀርባል።የህያዋን ቅሪት (Organic Matter) ተብላልቶ ወደ ሂዩመስ በሚቀየርበት ጊዜ በውስጡ ያሉ ንጥረ ነገሮቹ ሰብሉ ሊጠቀምባቸው በሚችል መልኩ ስለሚቀየሩ በቀላሉ በውሃ በመሟማት ጥቅም ላይ ይውላሉ።ከዚህ በተጨማሪም ሂዩመስ የአፈር አሲዳማነትን ኒውትራላይዝድ የማድረግ አቅም ስላለው ሰብሉ በጥሩ ሁኔታ ያድጋል።
*
2/ኮምፖስት የአፈሩን ቅርፅ ያሻሽላል።ሂዩመስ በአፈር ( በተለይም በአሸዋማ )ውስጥ የአሸዋ ጠጣሮችን እንዲጣበቁ ያደርጋል፣ይህም በጠጣሮች መካከል የሚኖረውን ቀዳዳ በማጥበብ የአፈሩን ውኃ ይዞ የማቆየት ችሎታ ያሻሽላል፣ስለዚህም የውኃና የአየር ይዘቱ የተመጣጠነ ይሆናል ወይም ይመጣጠናል።በመረሬ ወይም ዋልካ አፈር ውስጥ ያሉትን የሸክላ ጠጣሮች በመክበብና በመለያየት ተጣብቀው የመቅረት ባህሪያቸውን ይቀንስና በመካከላቸው ሰፋ ያሉ ቀዳዳዎችን ይፈጥርላቸዋል።በዚህም ምክኒያት የአፈሩን አየር የማስተላለፍ ችሎታ ያሻሽላል፣የውኃና የአየር ይዘቱ ይመጣጠናል።ከዚህም በተጨማሪ በሂዩመስ ምክኒያት የአፈሩ የውስጥ ቅርፅ ሲሻሻል መሬቱ ቢታረስም ባይታረስም የእፅዋት ስሮች ዘልቀው እንዲገቡ አመቺ ይሆናል።
*
3/የአፈሩን እርጥበት የመያዝ ችሎታ ያሻሽላል።በትክክል የተዘጋጀ ኮምፖስት የሂዩመስ መጠኑ ከፍተኛ ስለሆነ የእስፖንጅነት ባህሪ አለው።በዚህ ምክኒያትም ውኃንና የዕፅዋት ንጥረ ነገሮችን በቀላሉ ይቋጥራል፣አንድ ኪሎ ግራም ሂዩመስ እስከ 6 ሊትር ውኃ ድረስ ሊይዝ ይችላል ሳይንሱ እንደሚለው ከሆነ።ይህም በዝናብ ወቅት የወረደው ውኃ በብዛት ወደ አፈሩ ውስጥ ስለሚሰርግ |ጎርፍ |ይቀንሳል፣የከርሰ ምድር ውኃ ስለሚጨምር ምንጭና ውኃ ማቆሪያዎች ዝናብ በሚያቆምበት ወቅትም ቢሆን በቀላሉ አይደርቁም።
*
4/አረምን ፣ተባይንና በሽታን ለመቆጣጠር ይረዳል።አረሞች ለኮምፖስት ማዘጋጀት በሚውሉበት ጊዜ በዝግጅት ወቅት የሚፈጠረው ከፍተኛ ሙቀት የአረሙን ዘር በመቀቀል ይገድላል።በተመሳሳይ መልኩ የሰብል ቃርሚያ ለኮምፖስት ስንጠቀም በውስጥ ያለው በሽታና ተባይ ስለሚሞት የሚቀጥለው ሰብል አይበከልም።
*
5/በውኃና በነፋስ አፈሩ እንዳይሸረሸር ይጠብቃል።ኮምፖስት የአፈሩን ውኃ የማስረግ አቅሙን ስለሚጨምር ሊሸረሸር የሚችልን ፈሳሽ ውኃ ይቀንሳል።ከዚህም በተጨማሪ ሂዩመስ የአፈርን መጣበቅ ስለሚጨምር በቀላሉ በነፋስም ሆነ በሌላ ተንቀሳቃሽ አካል አይጠረግም።
*
6/የአርሶአደሩን ገንዘብ ያድናል።ኮምፖስት ያለምንም የገንዘብ ወጭ አርሶአደሩ ጉልበት ብቻ ሊዘጋጅ የሚችል ስለሆነ ኬሚካል ማዳበሪያ ከመበደር ከሚመጣ ዕዳ ያድናል።ከዚህ በተጨማሪ ኮምፖስት በአፈር ውስጥ በተፈጥሮ የአፈር ለምነትን ሊያሻሽሉ የሚችሉ ማይክሮ ኦርጋኒዝመስ ምግብ በመሆኑ የመሬት ለምነትን በዘላቂነት እንዲሻሻል ያደርጋል።በአሁኑ ጊዜ በዓለም ገበያ ያለው የኦርጋኒክ ምግብ ተፈላጊነት ኮምፖስት ተጠቅሞ ሰብል ለሚያመርት አርሶ አደር የተሻለ ገቢን ያስገኛል። ምንጭ፡ አግሪካልቸር ዴይሊ ፖስት
መረጃዎቻችንን፦
በፌስቡክ፡- @ethiocta
በቴሌግራም፡- https://t.me/ECTAuthority
በድረገጽ፡- https://www.etiocta.gov.et
ዩቲዩብ፡- https://www.youtube.com/@ethiopiancoffeeandteaautho1042
ተከታተሉን:: እናመሠግናለን