የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አካዳሚ በቡና ቅምሻና ደረጃ አወጣጥ ያሰለጠናቸውን ሠልጣኞች አስመረቀ
***********
የኢትዮጵያ ምር ገበያ በቡና ቅምሻና ደረጃ አወጣጥ ላይ ያሰለጠናቸውን 51 ሰልጣኞችን ሐምሌ 21 ቀን 2017 ዓ.ም በንግድና ቀጣናዊ ተስስር ሚኒስቴር ንግድ አዳራሽ አስመርቋል፡፡ በምርቃ ሥነስርዓቱ ላይ በክብር ዕንግድነት የተገኙት ክቡርት ወ/ሮ ያስሚን ወሀብረቢ የንግድ ትስስርና ወጪ ንግድ ፕሮሞሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ለተመራቂዎቹ የእንኳን ደስ ያላችኹ መልዕክት አስተላልፈው፤ በያዝነው በጀት ዓመት በወጪ ንግድ ታሪካዊና እመርታዊ ውጤት መመዝገቡን አስታውቀዋል፡፡
ብዝኅ ምርትን የማሳደግና የጥራት ጉዳይ የውጭ ምንዛሪን ለማሳደግና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በትኩረት የሚሰራበት መስክ መኾኑን ገልጸው የጥራት ሰልጣኞችም ሀገራችን በጥራት ላይ ያላትን ተወዳዳሪነት ለማስፋት የሚኖራቸው ሚና ጉልኽ ነው ብለዋል፡፡
ሚንስትር ዴኤታዋ አክለውም የሀገራችንን ኋለቀር የግብርና ምርቶች የግይብት ሥርዓትን በዘመናዊ የግብይት ሥርዓት በመተካት አርሶ አደራችን በቀጥታ ተጠቃሚ የሚኾንበት፤ በወጪ ንግዱ በጥራትና በብዝኅ ምርት ተወዳዳሪ እንድትሆን በማስቻል የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከፍተኛ ሚናውን እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል፡፡
አቶ መርጊያ ባይሳ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መድረኩን በእንኳን ደስ አላችኹ መልዕክት የከፈቱ ሲኾን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ያካበተውን የዘመናዊ ግብይት ሥርዓት ልምድ መሠረት በማድረግ የልህቀት ማዕከልነቱን በማጠናከር በዘመናዊ ግብይት የተለያዩ አሰራሮች ላይ ያተኮረ የምርምር፣ የስልጠናና ሰርተፊኬሽን እየሰጠ ይገኛል ብለዋል፡፡
አካዳሚው በሀገር ውስጥ ላሉ በቡና ቅምሻ፤ በጥራጥሬና ቅባት እህሎች የደረጃ አወጣጥ ላይ ስልጠና በመስጠት የሀገራችን ምርት ጥራት እድገት ላይ የበኩሉን አስተዋጸኦ እያደረገ እንደሚገኝና ከሀገር ውጭም ከአፍሪካ ሀገራት ለመጡ ሰልጣኞችም በምርት ገበያው የቢዝነስ ሞዴል ላይ ስልጠና በመስጠት ዛሬ ላይ ወደ ስምንት የሚጠጉ ሀገራት የግብርና ምርቶች ግብይት ስርዓት ልምድ በመቅሰም የራሳቸውን ገበያ ማደራጀት እንዲችሉ አቅም መፍጠር መቻሉን አስታውቃወል፡፡
ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተመራቂዎችም በሀገራችን ጥራትን የገበያ ቋንቋ በማድረግ በዓለም ገበያ በጥራት ተወዳዳሪ ምርቶችን ለመላክ የሚደረገውን ርብርብ ወደተሻለ ምዕራፍ የማድረስ አምባሳደራዊ ተልዕኮ እንዲወጡ አደራ ብለዋል፡፡
በመጨረሻም በስልጠና ኺደታቸው የላቀ አፈጻጸም ያሳዩ ሰልጣኞች ሽልማታቸውን ከክብርት ወ/ሮ ያስሚን ወሀብረቢ የንግድ ትስስርና ወጪ ንግድ ፕሮሞሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ተቀብለዋል ፡፡ሠልጣኞቹም የወጪ ንግድ ቋሚ ኤግዚብሽንን ጎብኝተዋል፡፡