አለማቀፋዊ ተወዳዳሪነትን ማረጋገጥ የሚቻለው ዘመናዊ እና ዲጂታላዊ አሰራርን በስፋት ተግባራዊ ማድረግ ሲቻል መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ነሀሴ 23/2017ዓ.ም
አዳማ
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ከኦሮሚያ ብ/ክልላዊ መንግስት ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ጋር በመተባበር የቡና፣ ሻይና ቅ/ቅመም የእሴት ሰንሰለት ዲጂታል ፕላትፎርም ዙሪያ ሰፋ ያለ ምክክር በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ የመድረኩ ዋና ዓላማ በተለይም በመረጃ አሰባሰብ እና ግብይት በኩል በተለምዶ ሲካሄድ የነበረውን አሰራር የበለጠ ማዘመን፣ ዓለማቀፋዊ ተወዳዳሪነትን ማረጋገጥ ስለሚቻልበት እና ዘመናዊ እና ዲጂታላዊ አሰራርን በስፋት ተግባራዊ ማድረግ ስለሚቻልበት ሁኔታ ለመመካከር ነው፡፡ ክቡር አቶ ሻፊ ዑመር የባለስልጣን መ/ቤቱ ምክ/ዋና ዳ/ር እና የግብይት ዘርፍ ኃላፊ፣ ክቡር አቶ ታጋይ ኑሩ የባለስልጣን መ/ቤቱ ምክ/ዋና ዳ/ር እና የልማት ዘርፍ ኃላፊ እንዲሁም ክቡር አቶ አህመድ ኢድሪስ በኦሮሚያ ብ/ክ/መንግስት የኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊን ጨምሮ ከ50 በላይ የሚሆኑ ከኦሮሚያ ብ/ክልላዊ መንግስት ፕሬዝደንት ጽ/ቤት፣ ከፌዴራል፣ ከክልሎች፣ ከማህበራት እንዲሁም ሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል፡፡
መድረኩን በቦታው ተገኝተው የከፈቱት ክቡር አቶ ሻፊ እንዳሉት ቡናን ከልጅነት እስከ እውቀት ስናመርተው፣ ስንጠጣው፣ ማህበራዊ ግንኙነታችንን ስናጠናክርበት፣ የውጭ ምንዛሬ ስናገኝበት እንዲሁም ስንዘምረው የነበረ ድንቅ ሀብታችን ፣ ለመላው አለም ያበረከትነውም ስጦታ ቢሆንም ማግኘት የሚገባንን ጥቅም በበቂ ደረጃ ለማግኘት ግን ብዙ ይጠበቅብናል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ዘርፉ ለዘመናት ከነበረበት ችግር እንዲላቀቅ ለማድረግ ተግዳሮቶቹን ከመለየት ጀምሮ፣ የተለያዩ ሪፎርሞች በማከናወን፣ ደንብ እና መመሪያዎች አውጥቶ ተግባራዊ ማድረግ በመቻሉ በተለይም በባለፉት 4 እና 5 አመታት አስደናቂ ለውጦች መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህም የሚመረተው ምርት፣ የመሬት ሽፋን እንዲሁም የኤክስፖርት አፈጻጸሞች ታሪካዊ በሚባል ደረጃ ለውጥ ማምጣታቸውን ገልጸው፤ ውጤቱ ለመምጣቱ ደግሞ ከአ/አደሩ እና ከክልሎች አንስቶ ሁሉም የዘርፉ አካላት ባደረጉት ርብርብ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ቡናን ብቻ ሳይሆን የሻይ እና ቅ/ቅመም ምርቶችንም ልዩ ትኩረት በመስጠት የውጭ ምንዛሬ ግኝታችንን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ክቡር አቶ ሻፊ፤ አለማቀፍ ተወዳዳሪነትን ጠብቆ አስተማማኝ ገበያ ለማግኘትም ዱካው የተጠበቀ ምርት ማቅረብ፣ በጥራት ማምረት፣ ምርቱን በወቅቱ ለገበያ ማቅረብ ላይ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ሰፊ ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በተለይም ዘመናዊ እና ዲጂታላዊ አሰራርን በስፋት ተግባራዊ ማድረግ ዘመኑ የሚፈልገው መሰረታዊ ጉዳይ በመሆኑ በዚህ ላይ መስራት እንደሚያስፈልግም አጽንዖት ሰጥተው አስምረውበታል፡፡
ክቡር አቶ አህመድ ኢድሪስ በበኩላቸው ኦሮሚያ ክልል ከውሀ፣ ሰፊ መሬት፣ በርካታ የሰው ሀይል በተጨማሪ በርካታ ሀብቶች ያሉት መሆኑን ጠቁመው ክልሉ በቀረጻቸው 29 ኢኒሺየቲቮች ስንዴ፣ ቡና እና ሻይ ቅጠልን ጨምሮ በሌሎችም ዘርፎች ተጨባጭ ለውጦች መምጣታቸውን አስረድተዋል፡፡ መካናይዝድ እና ዘመናዊ አሰራር መከተል በክልሉ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን የተናገሩት ክቡር አቶ አህመድ፤ ያረጁ ቡናዎችን በማደስ እና በመጎንደል፣ ግዙፍ የሻይ ልማት በማልማት አ/አደሩ የበለጠ ተጠቃሚ የሚሆንበት አሰራር ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በሻይ በኩል ያለውን አቅም ለመጠቀም ኢንዱስትሪ ላይ መሰራት ስላለበት ክልሉ ከባለሀብቶች እና አጋሮች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ያስረዱት ኃላፊው፤ እሴት የተጨመረባቸውን ምርቶች በዘመናዊ መንገድ ወደ አለም ገበያ ለማቅረብ እንዲሁም በዘመናዊ የመረጃ እና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም በኩል ያለውን ክፍተት ለመሙላት ባለስልጣን መ/ቤቱ ይህን መሰል መድረክ ማዘጋጀቱ የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የቡና፣ ሻይና ቅ/ቅመም የእሴት ሰንሰለት ዲጂታል ፕላትፎርም አጠቃላይ ሁኔታ እንዲሁም መልካም ተሞክሮን የተመለከቱ መነሻ ጽሁፎች በሰለጠኑ ባለሙያዎች የቀረቡ ሲሆን ሰፊ ውይይት ተካሂዶ ማጠቃለያ ተሰጥቶበታል፡፡
ክቡር አቶ ታጋይ ኑሩ በማጠቃለያ ንግግራቸው እንደተናገሩትም ዲጂታላይዜሽን ከዘመኑ ጋር ማራመድ የሚያስችል ዘመናዊ አሰራር እንደሆነና አለማችን በተለይም ከሰለጠነ አገራት ጋር ያለውን የግብይትም ሆነ መሰል መስተጋብር ለመፍጠር በተቻለ አቅም ሁሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም እኩል መራመድ ይገባል ብለዋል፡፡ በቀረበው የተለያየ ማብራሪያ መሰረት የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልል ፕሬዝደንት ጽ/ቤት በዚህ በኩል የተጓዘበት ርቀት የሚደነቅ መሆኑን እና በቀጣይ ባለስልጣን መ/ቤቱ በተለይም ኢዩዲአርን ተግባራዊ ለማድረግ እንዲሁም ሌሎች የቴክኖሎጂ እና ዘመናዊ መረጃ አያያዝ ስርአቶች ጋር ማስተሳሰር እና በቅንጅት ሊሰራ ቢችል የበለጠ ውጤታማነትን ማረጋገጥ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡