በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ካፋ ዞን ፣በገዋታ ወረዳ ቦጊንዳ ቀበሌ የሻይ ችግኝ ጣቢያ የችግኝ ዝግጅት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተከናወነ።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው መርሐ ግብሩን ባስጀመሩበት ወቅት፣በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ መሪነት የተጀመረው የሻይ ልማት ኢኒሼቲቭ በክልሉ ተግባራዊ ለማድረግ ተወስኖ በልዩ ትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
አያይዘውም፣ክልሉ ለሻይ ልማት ምቹ በመሆኑ በቅድሚያ በተለዩ አራት ዞኖች ማለትም ካፋ፣ሸካ፣ቤንችሸኮ እና ዳውሮ ዞኖች በስፋት ለማምረት ዕቅድ ተይዞ እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቅሰው ከዚህም ውስጥ በካፋ እና ቤንችሸኮ ዞኖች የሻይ ችግኝ ዝግጅት ጣቢያዎችን ስራ በማስጀመር የልማቱን ተግባራዊነት ለማረጋገጥ እየተሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
ዘንድሮ በክልሉ ተግባራዊ ከሚደረጉ ክልል አቀፍ ኢኒሼቲቮች መካከል አንዱ በገዋታ ወረዳ የሚገኘው የቦጊንዳ ሻይ ችግኝ ዝግጅት ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ እንዲቻል በልዩ ትኩረት እየተመራ እንደሚገኝ ጠቅሰው የካበተ ልምድ ያላቸው የውሽውሽ ሻይ ልማት ባለሙያዎች ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙም ክቡር አቶ ማስረሻ በላቸው አስረድተዋል።
በችግኝ ጣቢያው ውስጥ ለ5መቶ 22ሺህ 140 የሻይ ችግኞች የሚሆን የፖሊ አፈር ጥቅጣቆ ተጠናቆ ለተከላ ዝግጁ መደረጉን የተናገሩት የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ ናቸው።
ይህም 34 ሄክታር ማሳን እንደሚሸፍን ገልፀው ለውጤታማነቱም ዞኑ የሚጠበቅበትን ድርሻ እንደሚወጣም አረጋግጠዋል።
በካፋ ዞን አራት ወረዳዎች ላይ በ4 ችግኝ ዝግጅት ጣቢያዎች እስካሁን 1.8 ሚሊዮን ፖሊ የአፈር ጥቅጣቆ ስራዎች ተከናዉኗል ሲሉም አቶ እንዳሻው ከበደ ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አስራት መኩሪያ፣ ክልሉ በግብርናው ዘርፍ ለማሳካት እየሠራባቸው ካሉ ግቦች አንዱ የሻይ ቅጠል ኢኒሼቲቭ ልማት ድርሻ ከፍተኛ መሆኑንገልጸዋል።
የክልሉን የልማት ፀጋዎች በውል በመለየት ወደ ሚጨበጥ ሀብት ለመቀየር በተሰጠው ልዩ ትኩረት ከክልላችን የአየር ንብረት ብዝሃነት ጋር የሚስማሙ የሻይ ችግኝ ዝሪያዎችን በማዘጋጀት ለተግባራዊነቱ በመስራት ላይ እንገኛለን ብለዋል።
አክለውም፣አርሶ አደሮችን ከሻይ ቅጠል ልማት ተጠቃሚ በማድረግ ለሀገር ገቢን ለማስገኘት እንዲቻል በቁርጠኝነት መምራት እንደሚገባና የክልሉ መንግስት ለስኬታማነቱ በሁሉም ረገድ የማያቋርጥ ክትትልና ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
የገዋታ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አርገው ሀይሌ በበኩላቸው፣ወረዳው ያለው እምቅ ሀብት ለሻይ ልማት ተስማሚ እንደሆነና እስካሁን በሻይ ልማት እየታየ ያለው መልካም ጅማሮ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።
በሻይ ልማት ዝግጅት ጣቢያው ከ171 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው እና ከዚህም ውስጥ 150 የመሆኑት ሴቶች እንደሆኑም ጠቅሰዋል።
የቦጊንዳ የሻይ ችግኝ ዝግጅት ጣቢያው በዘላቂ መሬት አያያዝ ፕሮግራም (RLLP II) ኘሮጄክት ድጋፍ የተሰራ ሲሆን እንደ ክልል በሻይ ዘርፍ የተያዘውን ኢኒሼቲቭ ለማሳካት እንደሚረዳም ተጠቁሟል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸውን ጨምሮ ሌሎች የክልል፣የዞንና የገዋታ ወረዳ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
/