የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ዳዬ እና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዳዬ በንሳ የቡና ማቀነባበሪያ ፋብሪካን መርቀው ከፍተዋል፡፡
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው፣ ክልሉ በዳዬ በንሳ ቡና ላኪ ድርጅት እንቅስቃሴ ደስተኛ መሆኑን ገልጾ፣ በተሻለ ደረጃ የሀገራችንን ቡና እንዲያስተዋውቁ እና ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረግላቸዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገች ነው፤ ለመለወጧ የሚረዱ አገልግሎቶችም እየቀረቡ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ መንግስት፣ የግሉ ዘርፍ የልማት መሠረት እንደሆነ ያምናል፣ ለዚህም የተለያዩ ፖሊሲዎችን በማውጣት እና በመተግበር ዘርፉን እየደገፈ ይገኛል ብለዋል።
በቡና ምርት ላይ እሴት የሚጨምር ፋብሪካ በከተማችን በመመስረቱ ደስተኞች ነን፣ እንደ ከተማ አስተዳደርም ድርጅቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሀገራችንን ቡና ለማስተዋወቅ እና ተወዳዳሪ ለመሆን በሚያደርገው ጥረት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረግም ገልጸዋል።
የዳዬ በንሳ ቡና ላኪ ድርጅት አንዱ መስራች አቶ አሰፋ ዱካሞ፣ ድርጅቱ የቡና ምርት ላይ በስፋት እየሰራ እንዳለ ጠቅሰው፤ በ2017 ዓ.ም 8700 ቶን በላይ ቡና መላክ መቻሉን ገልጸዋ።
በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ከተማ የተመረቀው ዘመናዊ የቡና ማቀነባበሪያ በ2 ቢሊየን ብር የተገነባ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ዳየ በንሳ ቡና በዘርፉ ለ20 ዓመታት የቆየ እና የኢትዮጵያን ቡና በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ አበርክቶ እንዳለውም ገልጸዋል።
ዳዬ በንሳ ወደ 30 የዓለም ሀገራት ቡናን እየላከ ያለ ድርጅት መሆኑም ተመላክቷል፡፡
ዳየ በንሳ ቡና ላኪ ድርጅት 20ኛ የምስረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለዲቦራ ፋውንዴሽን እና ለህብረት ለበጎ አድራጎት ማህበር ለዕያንዳንዳቸው የአንድ አንድ ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል።






