የሞጆ አረንጓዴ ሎጂስቲክስ ማዕከል ማስፋፊያ ግንባታን በቀጣዩ ዓመት መጀመሪያ ወራት ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን አስታወቀ። ሞጆን ሁለን አቀፍ የሎጂስቲክስ ማዕከል ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን እና ወደቡን በቴክኖሎጂ የታገዘና ዘመኑን የዋጀ ሁለገብ የሎጅስቲክስ ማዕከል ለማድረግም የማስፋፊያ ግንባታ እየተከናወነ ነው ሲሉ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አብዱልበር ሸምሱ (ኢ/ር) ገልጸዋል፡፡
የሞጆ አረንጓዴ ሎጂስቲክስ ማዕከል ማስፋፊያ ግንባታ ሲጠናቀቅ አሁን ላይ ወደቡ ያለውን አቅም ከእጥፍ በላይ ማሳደግ እንደሚያስችል እና ከውጪ ከሚገባው እቃ 90 በመቶው በሞጆ ደረቅ ወደብ እንደሚስተናገድ ጠቁመው ፥ የወደቡን አሰራር በማዘመን የወጪና ገቢ ንግድን ለማቀላጠፍ በቁርጠኝነት ይሰራል ብለዋል፡፡አሁን ላይ የማስፋፊያ ግንባታው እየተገባደደ እንደሚገኝ ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ የማሽነሪ ተከላ ሥራው በቅርቡ ይከናወናል፡፡ የሞጆ አረንጓዴ ሎጂስቲክስ ማዕከል ግንባታ ሥራ አስኪያጅ ደሳለኝ ጌታሁን (ኢ/ር) በበኩላቸው ÷ፕሮጀክቱ የኢትዮ ጅቡቲን የንግድ ኮሪደር አቅም ከ95 በመቶ በላይ መሸከም እንዲችል ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን እና የፕሮጀክቱ የሲቪል ሥራ አሁን ላይ 90 በመቶ መድረሱን አስታውቀዋል፡፡