አዲስ አበባ:ሀምሌ 10/2017ዓ.ም የመጋዘን ደረሰኝ ስርዓት የግብርና ኢኮኖሚያችንን ለማሸጋገርና በኢትዮጵያ የገጠር ልማትን በማጎሎበት የህብረተረቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር የንግድ ትስስርና የወጪ ንግድ ፕሮሞሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ያስሚን ውሃቦረቢ ገለፁ።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የመጋዘን ደረሰኝ ስርዓት ተግባራዊነትና እያጋጠሙ ባሉ ችግሮች እንዲሁም መፍትሄዎቹ ላይ ያተኮረ ውይይት ከባንኮችና የፋይናንሻል ተቋማት ሃላፊዎችና ተወካዮች ጋር በዛሬው እለት ውይይት ተካሄዷል።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ክብርት ወ/ሮ ያስሚን ውሃብረቢ በሀገራችን የመገዘን ደረሰኝ ስርዓት የማስፈፀሚያ አዋጅ ወጥቶለት በሙከራ ደረጃ መተግበር ከጀመረ 20 ዓመታትን ቢያስቆጥርም ተቆጣጣሪ አካልና ባለቤቶ ተቋም ስላልነበረው የአፈፃፀም አድማሱና ያስገኘው ው ውጤት ውስን ሆኖ ቆይቷል ያሉ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ግን መንግስት ስርዓቱ ለእድገታችን የሚኖረውን ሚና በመረዳት ተቆጣጣሪና ባለቤት ተፈጥሮለት ለስራው መቀላጠፍና መተማመንን ለማጎልበት በሚያግዙ ደንቦችና መመሪያዎች እንዲደገፍ ተደርጎ በተሻለ ሁኔታ እየተተገበረ ይገኛል ብለዋል።
የውይይቱ ዓላማ በመጋዘን ደረሰኝ ስርዓት የተገኙ ውጤቶችን ለመዘከር ብቻ ሳይሆን ስርዓቱን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግና እያጋጠሙ ባሉ ተግዳሮቶች ዙሪያ በተለይም የፋይናንስ ተቋማትን ቁርጠኝነትና ተሳትፎ በጥልቀት በመፈተሽ በቀጣይ የተሻለ ስራ ለመስራት የሚያስችል የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ እንደሆነ ሚኒስትር ዴኤታዋ አንስተዋል።
አያይዘውም የመጋዘን ደረሰኝ ስርዓት አርሶ አደሮች፣የህብረት ስራ ማህበራት፣ የግብርና ምርት አቀናባሪዎችና ነጋዴዎች ምርታቸውን በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲያከማቹ፣የተከማቸ ምርታቸውን ተጠቅመው ብድር እንዲያገኙና መቼና እንዴት እንደሚሸጡ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ እንዲወስኑ የሚያስችል የተረጋገጠ መሣሪያ መሆኑን አስረድተዋል።
በመድረኩ የተለያዩ ሰነዶችና ልምዶች ቀርበው ውይይት የተካሄደ ሲሆን በመጨረሻም ክብርት ወ/ሮ ያስሚን ከማን ምን እንደሚጠበቅ አቅጣጫ በማስቀመጥ ውይይቱ ተጠናቋል።
ዘገባው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ነው።