የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ከባለስልጣኑ የቡና ማሰልጠኛ ማዕከል እና የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት /UNIDO/ ጋር በመተባበር "ከድንበር ባሻገር ንግድ እና እድገት" በሚል ርዕስ ስልጠና በማዕከሉ አዳራሽ በመስጠት ላይ ይገኛል ።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የተከበሩ ዶ/ር አዱኛ ደበላ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለፁት ወቅታዊ መረጃዎችን ለመለዋወጥ በተለይም ደግሞ ለቡና አቅራቢዎች እና ላኪዎች አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻልበትና ምርታቸውን መቸ እና የት መሸጥ እንዳለባቸው እንዲሁም የትኛውን ሎጀስቲክስ ሊጠቀሙ እንደሚገባ የሚያግዝ ስልጠና ነው ብለዋል፡፡የባለስልጣን መ/ቤቱ በዚህ ረገድ በየጊዜው መረጃዎችን ተደራሽ የሚያደርግ መሆኑን ገልፀው ይህን ስራችን ለማቅለል በሚረዳው በኢ-ኮመርስ እና በሎጀስቲክስ ዙሪያ ስልጠና ለመውሰድ ስለመጣችሁ ከልብ አመሰግናለሁ ብለዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ባለስልጣን መ/ቤቱ ከልማቱ እስከ ግብይቱ ያሉትን የእሴት ሰንሰለት የሚቆጣጠርና የሚከታተል ዕውቅና ያለው ተቋም ነው ብለዋል፡፡ በተለይም ለልማቱ ተግዳሮት የሆኑትን የግብይት ሂደት ችግሮችን ለይቶ በማውጣት በስፋት እየተሰራበት መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ ዶ/ር አዱኛ ከሎጀስቲክስ እና ኢ-ኮመርስ አንፃር በባለስልጣን መ/ቤቱ የተቋቋመ ቡድን መኖሩን ጠቁመው የገበያ መረጃ፣ የጉምሩክ እና የመሳሰሉ በርካታ ስራዎች በመሰራት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ በተለይም ከሎጀስቲክስ ጋር እየሰሩ ካሉት በርካታ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በመጨረሻም እንዲህ አይነት ስልጠና የበለጠ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግና ስራዎችን በማቅለል በኩል የሚያግዝና ተጨማሪ ግብዓት በመሆኑ ዲ.ኤች ኤል/DHL/ ከዩኒዶ ጋር በመተባበር ስልጠናውን ለመስጠት ባለስልጣን መ/ቤቱን መርጦ በመምጣቱ በእጅጉ አመስግነው ስልጠናውን በይፋ ከፍተዋል፡፡
ስልጠናው በዋናነት በኦንላይን የሚሰጥ ሆኖ ለጥቃቅንና አነስተኛ የስራ ፈጣሪዎች /SMEs/ ፣ ለቡና ላኪዎች፣ለቡና አምራች ማህበራት እና በቡናው ኢንዱስትሪ ተዋናይ ለሆኑ ሁሉ በእጅጉ ጠቃሚ ሲሆን በኢ-ኮሜርስ ዲጂታል ቻናሎች እና የሎጂስቲክስ ሚና በይዘት ትኩረት ያደረገና በተለይም ለኢትዮጵያውያን ስራ ፈጣሪዎች የድንበር ተሻጋሪ ንግድን ለማሳደግ ያስፈልጋል መባሉን የባለስልጣን መ/ቤቱ የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ቡድን በቦታው ተገኝቶ ዘግቦታል ።
መረጃዎቻችንን፦
በፌስቡክ፡- @ethiocta
በቴሌግራም፡- https://t.me/ECTAuthority
በድረገጽ፡- https://www.etiocta.gov.et
ዩቲዩብ፡- https://www.youtube.com/@ethiopiancoffeeandteaautho1042
ተከታተሉን:: እናመሠግናለን