ከእርሻ እስከ ኤክስፖርት የቡና ዱካ መከታያ ቴክኖሎጂ ላይ ውይይት ተካሄደ
Back

ከእርሻ እስከ ኤክስፖርት የቡና ዱካ መከታያ ቴክኖሎጂ ላይ ውይይት ተካሄደ

ECTA
5 min read

ነሐሴ 20/2017 ዓ.ም

አዲስ አበባ፤

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የቡና ዱካን ለመከታተል የሚያስችል ቴክኖሎጂን ለማስበልጸግ ያዳራጀውን ታስክ ፎርስ የውይይት መድረክ በመጥራት ቩልካን በተባለ አገር በቀል የግል ድርጅት የበለጸገውን ሲስተም ላይ ውይይት እንዲካሄድ አድርጓል፡፡ ታስክፎርሱ ላለፉት ሁለት አመታት በስራ ላይ የቆየ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን በበለጸገውና በዳበረው  ሲሰስተም ላይ ሁለት ጊዜ ተሰብስቦ እንደተወያየና ይህ ለሶስትኛ ጊዜ የተጠራ የውይይት መድረክ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ 

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ቡና ሻይ ባለስልጣን የኢንፎርሜሽንና ኮምዩኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ እንዲሁም የትሬሴቢሊቲ ፕሮጀክት አስተባባሪ ወ/ሮ ሐዊ አቶምሳ ሲሆኑ በንግግራቸው ታስክፎርሱ ውስጥ በቡና የእሴት ሰንሰለት ውስጥ የየራሳቸው ድርሻ ያላቸው አካላት እንደተካተቱና በእዚህም መድረክ እነዚህ አካላት ተገኝተው ሀሳብ እንዲሰጡ እንደተጋበዙ ገልጸዋል፡፡ የትሬሴቢሊቲ ሲስተሙ ቩልካን በመባል የሚታወቅ ድርጅት ሲያበለጽግ እንደቆየ አስታውሰው ድርጅቱ ከባለስልጣኑ ጋር የስምምነት ሰነድ ተፈራርሞ ወደስራ እንደገባ አስታውሰዋል፡፡ ታዳሚዎቹ በቡና የእሴት ሰንሰለት ውስጥ ያሉ አካላት በሙሉ የተጋበዙበት ስለሆነ በሰንሰለቱ መካከተት ያለባቸውና በሲስተሙ መታከል ያለባቸው ነገሮች አካታች በሆነ መልኩ ገንቢ አተያየቶች እንደሚሰነዘሩ ተስፋቸውን ገልተዋል፡፡ 

ይህን ካሉም በኋላ ሲስተሙን በተመለከተ ሲናገሩ ከቡና ጥራት ባሻገር የልማት ዘርፉ ጉዳይ  እንዲጨመር መደረጉን ተናግረዋል፡፡ በማከልም ከአውሮፓ ኅብረት ከደን ጭፍጨፋ ነጻ ደንብ ጋር በተያያዘ ደግሞ የተሰበሰቡ ዳታዎች የሚከማችበት ሴንትራላይዝድ የሆነ ስርዓት እንደተካተተበት ተናግረዋል፡፡ ስለሆነም ሙሉ ለሙሉ የቡናን ዱካ ለመከታተል የሚያስችል ሲስተም ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ሲስተሙም ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ መስክ በመውጣት ውጤታማነቱ የሚታይ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ 

ከእሳቸው ንግግር በኋላም ቩልካን ያበለጸገውንና ያዳበረውን ሲስተም አቅርቧል፡፡ ቴክኖሎጂው ከባለስልጣኑ ጋር በተደረገ ስምምነት መሠረት በልጽጎ በሁለት መድረኮች ውይይት እንደተደረገበት አስታውሰው በተሰበሰበው ግብአት መሰረት ከአውሮፓ ኅብረት የደን ጭፍጨፋ ነጻ ደንብ አንጻር መታከል ያለባቸው ነገሮች እንዲጨመሩ በቀረበው ሃሳብ መሠረት ለዚያ በሚያመች መልኩ የማዳበር ስራ ተሰርቷል ብለዋል፡፡ ስለሆነም የማዳበሩ ዓላማ ከኅብረቱ ዓላማ ጋር ባማከለ መልኩ ማድረግ ነው ብሏል፡፡ ከዚህም ባሻገር ተጠያቂነትን የሚያሰፍን ሲስተም እንደሆነ ገልጸው የቡና ሂደቱ በእያንዳንዱ የእሴት ሰንሰለት ደረጃ ምን ይመስላል የሚለውን የሚያሳይ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ 

ሲስተሙ ላይ የታከሉትን ገጽታዎች ሲያቀርቡም የቡና ተዋናዮች የሚመዘገቡበት ክፍል፤ የቡና እርሻ ካርታ ከጂፒኤስና ከፖሊገን መውሰድን የሚያስችል፤ የአምራቾች እና የቡና ማሳ መመዝገቢያ፣ የሞባይል መተግበሪያ አፕልኬሽን፣ የሽኝት ጣቢያ ሽኝት በሚያካሂዱበት ወቅት ያለውን ሂደት መከታተያ፣ የመጋዘንና የንብረት መቆጣጠሪያ፣ የጥራት መቆጣጠሪያ ሞጁል፣ QR ማረጋገጫ ያለው የላኪዎች ገጽ፣ አድሚኖች የሚጠቀሙበት የባካፕና ሬስቶር ገጽ እና ለሪፖርት ጠቀሜታ የሚውሉ መሳሪያዎች እንደተጨመሩበት ገልጸዋል፡፡ 

በስተመጨረሻም የባለስልጣኑ የኢዩ ካፌ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ፍቅሩ አመኑ መድረኩን በንግግር ዘግተዋል፡፡ በንግግራቸው ስጋቶችን በጥናት ተደግፎ ልየታ መካሄድ ላይ ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል፡፡ የበለጸገውና የዳበረው ቴክኖሎጂም ለራሳችን ስንል ብቻ ሳይሆን ካለው የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ጋር አብሮ መጓዝ ግድ የሚል ስለሆነ ወደኋላ መመለስ አይገባም ሲሉ አሳስበዋል፡፡ በመድረኩም በተሰነዘሩት ሃሳቦች መሠረት ሲስተሙን የማጥራት ስራ እንዲሰራ አክለው አሳስበዋል፡፡ በቀጣይም ለቴክኖሎጂው ይበልጥ መዳበር ኤክስፖርተሮችን ጨምሮ ሁሉም የቡና ተዋናዮች ተሳትፎ እንዲሚያሻ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ ባለስልጣን መስሪያቤቱ ስራውን እዚህ አድርሷል፤ እስከመጨረሻም ይገፋበታል ብዬ አምናለው ሲሉ እምንታቸውን ገልጸዋል፤ እስካሁን እየደከሙ ያሉትንም አካላት አመስግነዋል፡፡

Gallery

Gallery image 1
Gallery image 2
Gallery image 3
Gallery image 4
Gallery image 5
Gallery image 6

Tags

#ecta#digital app