የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በስርዓተ ጾታ ዙሪያ የተዘጋጁ ሰነዶችን ለሚመለከታቸው ባለድርሻና አጋር አካላት በማቅረብ ውይይት እንዲካሄድባቸው አድርጓል። በመድረኩም ክቡር አቶ ሠፊሳ አባቡ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ጽ/ቤት ኃላፊ፣ ክቡር አቶ መስፍን ቃሬ የሲዳማ ክልል ቡናና ፍራፍሬ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር፣ ክቡር አቶ ዓማኑኤል ብሩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር፣ ክቡር አቶ አሕመድ አበል-ማረፍ የኦሮሚያ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ተገኝተውበታል።
በመድረኩም ክቡር አቶ መስፍን ቃሬ እንግዶቻቸውን እንኳን ደህና መጣችሁ ካሉ በኋላ ቡና ከፍተኛ ገቢ በማስገኘት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው ይህም የሆነው በተደረገው የምርትና ምርታማነት ማሻሻያና ግብይቱ ላይም በተሰሩ ስራዎች እንደሆነ አውስተው በዚህም ቀደም ሲል ከቢሊዮን ዶላር በታች ሲገኝ የነበረው ገቢ በቢሊዮኖች እየተገኘ እንደሆነ ጠቅሰዋል። ውጤቱም በዘርፉ ለሚገኝ አካል ሁሉ ትልቅ ስኬት ነው ካሉ በኋላ ምስጋና ይገባል ሲሉ ደስታቸውን ገልጸዋል።
በማስከተልም ቡና በስፋት በሚመረትባቸው አካባቢዎች ያለው የልማት እንቅስቃሴ የቡና ውጤት ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ከላይ ለተጠቀሱት ከፍተኛ ውጤቶች ሁሉ ቡናን በማምረትና በምርታማነቱ የሴቶች ተሳትፎ ቀላል አይደለም ሲሉ አድንቀዋል። በክልሉ ባሉ 51 ኢንዱስትራዎች 75 በመቶው የቡና ዝግጅት የሚከናወነው በሴቶች ነው ብለዋል።
መድረኩም ጠቃሚ የልምድ ልውውጥና የግንዛቤ ሽግግር የሚደረግበት እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸው በድጋሚ እንግዶቻቸውን እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል።
በማስከተል ንግግር ያሰሙት ክቡር አቶ ሠፊሳ አባቡ ሲሆኑ በመክፈቻ ንግግራቸው በተለያዩ የቡናው ርዕሰ ጉዳዮች መነጋገር ቀላል እንዳልሆነ ገልጸው በየአመቱ እየተመዘገበ የመጣው አዳጊ የውጭ ቡና የገቢ ግኝት ቀላል እንዳልሆነና በዚህም በተያዘው ዓመት 2.6 ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል ሲሉ አብስረዋል፤ የውጤቱ ባለቤቶችም ሁላችንም ነን ብለዋል። አያይዘውም ይህን ውጤት ይዘን ስርዓተ ጾታን መሠረት ባደረገ መልኩ ለመነጋገር እዚህ ተገኝተናል ሲሉ ተናግረዋል። ስለሆነም የሴቶች ተጠቃሚነት፣ እኩልነትና አካታችነት የተመለከቱ የተለያዩ ሰነዶች ተዘጋጅተዋል ያሉ ሲሆን ሰነዶቹ ቀላል ሰነዶች እንዳልሆኑና ክልሎች ወስደው የዕቅዳቸው አካል በማድረግ ወደሕዝቡ ማውረድ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
ከንግግሮቹ በኋላም ሰነዶቹ ማለትም የስርዓተ ጾታ ስትራቴጂ፣ የግብይት ስትራቴጂ ከስርዓተ ጾታ አንጻር፣ በስርዓተ ጾታ ላይ የተካሄደ የጥናት ሰነድ የቀረቡ ሲሆን ከኮለምቢያ የቡና ሴክተር የሴቶች አሳታፊነትና ተጠቃሚነት ተሞክሮ በአቶ ፍጹም መንገሻ የባለስልጣኑ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ስራ አስፈጻሚ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶባቸዋል።