ከEUDR ጋር በተያያዘ በመረጃ አሰባሰብ እና የመረጃ ቋት አስተዳደር ዙሪያ ስልጠና በመሠጠት ላይ ነው!!!
Back

ከEUDR ጋር በተያያዘ በመረጃ አሰባሰብ እና የመረጃ ቋት አስተዳደር ዙሪያ ስልጠና በመሠጠት ላይ ነው!!!

Ethiopian Coffee And Tea Authority
5 min read

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አውሮፓ ህብረት ከቡና ጋር በተያያዘ በቅርቡ ተግባራዊ ሊያደርገው ባሰበው መመሪያ ላይ በመረጃ አሰባሰብ እና የመረጃ ቋት አስተዳደር ዙሪያ በጅማ ከተማ ስልጠና በመሠጠት ላይ ነው።

በስልጠናው ላይ ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞን እና ወረዳዎች፣ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ከጋምቤላ እና ቤንሻንጉል ጉምዝ የተውጣጡ 100 የሚጠጉ የስራ ሃላፊዎች እና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ። በቀጣይ ተከታታይ አምስት ቀናትም በዘርፉ ላይ ሰፊ ልምድ እና ዕውቀት ባላቸው ባለሙያዎች በንድፈ ሀሳብ እና በተግባር የተደገፈ ስልጠና እንደሚሰጥ ተገልጿል።

መድረኩን በይፋ የከፈቱት ክቡር አቶ ደጀኔ ሂርጳ የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክ/ኃላፊ ናቸው። አቶ ደጀኔ ቡና ለኢትዮጵያ የጀርባ አጥንት ብቻ ሳይሆን ደምም ነው ያሉ ሲሆን በተለይ ከባለፈው 4 አመታት ወዲህ በቡና ኤክስፖርት እየመጣ ያለው ለውጥ አስደሳች እና የሚደነቅ መሆኑን እና በታሪክ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው 2.65 ቢሊዮን ዶላር የሁሉም በየደረጃው የሚገኙ የዘርፉ ተዋናዮች መናበብ እና ቅንጅት ውጤት በመሆኑ እንኳን ደስ ያለን ብለዋል።

አቶ ደጀኔ እንዳሉት የቡና መሬት ሽፋን መጨመር፣ ምርታማነት ማደግ፣ የገቢ መጨመር ዋናው እና መሠረታዊ ጉዳይ ቢሆንም ከታች ከአ/አደር ማሳ ጀምሮ ያሉ እያንዳንዳቸው መረጃዎች በአግባቡ መያዝ እና መሰነድ ካልቻሉ ከዘመኑ ጋር እኩል ለመራመድ ስለሚያስቸግር ለጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶት በዚህ ደረጃ ስልጠና መዘጋጀቱን አድንቀዋል። EUDR ባወጣው መመሪያም መሠረት ጉዳዩ ከዚህ ጋር በቀጥታ የሚያያዝ በመሆኑ ጥራት ያለው፣ ተዓማኒ፣ ሙሉ ሽፋን ያለው እና ዘላቂ መረጃዎች በማሰባሰብ የአውሮፓን የቡና ገበያ አስተማማኝ ደረጃ ማድረስ እንደሚገባ ተናግረዋል። ሰልጣኞች የቀሰሙትን ዕውቀትም በትክክል ወደ ታች አውርደው ተግባራዊ ማድረግ እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።

ክቡር ዋና ዳይሬክተሩን ወክለው የተገኙት ወ/ሮ ሀዊ አቶምሳ በበኩላቸው ይህ ስልጠና ቀደም ሲል በሀዋሳ ከተማ መዘጋጀቱን እና በአቅራቢያው ያሉ ክልሎች የተሳተፉበት እንደሆነ ጠቁመዋል። EUDR መመሪያ በተመለከተ በሁሉም የቡና ቤተሰብ እና ባለሙያዎች በኩል ግንዛቤ እንደሚኖር ያላቸውን ተስፋ ገልፀው፤ ሆኖም ግን በጉዳዩ ላይ አስተማማኝ ግንዛቤ እንዲኖር እና በተለይም ደግሞ አውሮፓ ህብረት በቅርቡ ተግባራዊ ለማድረግ በተዘጋጀበት መመሪያ ላይ የሞባይል አፕሊኬሽን እና GPS መተግበሪያ በመጠቀም እንዴት Geo spacial Data ማሰባሰብ እንደሚቻል መሠረታዊ ስልጠና መስጠቱ ተገቢ በመሆኑ ባለስልጣን መ/ቤቱ ከEU CAFE ጋር በመተባበር ማዘጋጀቱን አስረድተዋል።

ከዚሁ ጋር የተያያዙ ስራዎች ከግብርና ሚ/ር፣ GIZ  እና ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሺያል ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ሰፋፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል።

አቶ ፍቅሩ አመኑ የ EU CAFE ፕሮጀክት አስተባባሪ ደግሞ አጠቃላይ EUDR ምንድነው፣ ከኢትዮጵያ ምን ይጠበቃል፣ የተቀመጡት ህጎችስ ምን ይመስላሉ፣ ህጎቹ በአግባቡ ባይተገበሩ ምን ችግሮችን ይዞ ይመጣል እና ሌሎችንም በጥልቀት ስልጠና ሰጥተዋል።

ይህን ስልጠና በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን EU CAFE ፕሮጀክት ያዘጋጀው ሲሆን ፕሮጀክቱ ባለፉት ተከታታይ አራት አመታት ፕሮጀክቱ ተግባራዊ በሚደረግባቸው ክልሎች እና ወረዳዎች ትራክተሮች፣ የመስክ ተሽከርካሪዎች፣ ሞተር ሳይክሎች፣ ኮምፒውተሮች፣ ስማርት ፎን እና ሌሎች ቁሳቁሶችን፤ ከዚህ በተጨማሪ አ/አደሩ ቡናውን ለማምረት የሚያስችሉት በርካታ የግብርና ግብዓቶች ሲያሰራጭ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን አ/አደር ማሳ ት/ቤቶችን በማቋቋም እና በማጠናከር አይነተኛ ሚና ሲጫወት መቆየቱ የሚታወስ ነው።

መረጃዎቻችንን፦

በፌስቡክ፡- @ethiocta

በቴሌግራም፡- https://t.me/ECTAuthority

በድረገጽ፡- https://www.etiocta.gov.et

ዩቲዩብ፡-  https://www.youtube.com/@ethiopiancoffeeandteaautho1042

ተከታተሉን::  እናመሠግናለን

Gallery

Gallery image 1
Gallery image 2
Gallery image 3
Gallery image 4
Gallery image 5
Gallery image 6

Tags

#ethiopian coffee and tea authority#eudr#coffee#amharic#ecta