ኢትዮጵያ የቡና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት የጀመረቻቸው ሥራዎች ውጤታማ ሆነዋል
Back

ኢትዮጵያ የቡና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት የጀመረቻቸው ሥራዎች ውጤታማ ሆነዋል

Ethiopian coffee and tea authority
5 min read

ኢትዮጵያ የቡና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት የጀመረቻቸው ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለፁ።

ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብ ሥርዓት ጉባዔ የተግባር ቀን በሚል ስያሜ ዛሬ ተጀምሯል።

የጉባዔው ተሳታፊዎች ኢትዮጵያ በምግብ ሥርዓት ሽግግር እያከናወነቻቸው የሚገኙ ተግባራትን በአዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ ውጪ በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

በሳይንስ ሙዚየም የተካሄደው የአፍሪካን የቡና እሴት ሰንሰለት ሽግግርን ማሳደግ ላይ ያለመ  የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

ለቡና ምርት፣ማቀነባበር እና ንግድ ሂደት የሚያስፈልግ ዘላቂ የፋይናንስ አማራጮችን መፍጠርና ቴክኖሎጂን ማስፋት በዘርፉ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት ወሳኝ መሆኑ ነው በመድረኩ የተነሳው።

በውይይቱ ላይ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ የተመድ ምክትል ዋና ጸሃፊ አሚና መሃመድ፣የዩጋንዳ ምክትል ፕሬዚዳንት ጀሲካ አሉፖ፣የፋኦ ዋና ዳይሬክተር ኩ ዶንግዩ፣ የጣሊያን ውጭ ጉዳይና ዓለምአቀፍ ትብብር ሚኒስቴር የልማት ትብብር ዳይሬክተር ጄነራል ስቲፋኖ ጋቲ፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ዓለምአቀፍ ተመራማሪዎች የግል ዘርፉ ተወካዮች ታድመዋል።

በዚሁ ወቅት የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ቡና ለኢትዮጵያውያን ብሎም ለአፍሪካ የግብርና ምርት ብቻ አይደለም። ከታሪክ፣ ከማንነትና ከኢኮኖሚ ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት ያለው ስትራቴጂክ ምርት ነው።

የቡና መገኛዋ ኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት የጀመረቻቸው ሥራዎች ውጤት እያስገኙ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።

የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቋቋም የሚችል ምርት በማምረት ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆኑ በትኩረት መሰራቱንም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ገበያ ያለው ተፈላጊነትና ተወዳዳሪነት እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው፤ይህም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ መሆኑን አብራርተዋል።

የተመድ ምክትል ዋና ፀሃፊ አሚና ጄ. መሃመድ በበኩላቸው፤ ቡና የበርካታ ዜጎች መተዳደሪያ መሆኑን አንስተዋል።

በተለይም አነስተኛ ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮች ህይወት የተመሰረተው በቡና ምርት ላይ መሆኑን አመልክተው፤ የዘርፉን ምርትና ምርታማነትን ማሳደግና እሴት መጨመር የበርካታ ሰዎችን ኑሮ ለማሻሻል እንደሚችል ገልጸዋል።

የቡና እሴት ሰንሰለት ሽግግርን ለማምጣት ፋይናንስና ኢንቨስትመንትን ማሳደግ ቴክኖሎጂን በስፋት መጠቀም የገበያ ዕድሎችን ማስፋት እንደሚገባ አመልክተዋል።

የዩጋንዳ ምክትል ፕሬዚዳንት ጀሲካ አሉፖ በበኩላቸው፤ ቡና ለዩጋንዳና ለበርካታ አገራት የግብርና ማንነትና የአገር አቀፍ የልማት ግብ አካል ነው።

ዘላቂ፣አስተማማኝና አካታች የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አገራቸው የተለያዩ እርምጃዎች  እየወሰደች መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በዚህም የቡና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ምርት በዓይነትም በጥራትም ጨምሯል ነው ያሉት።

የቡና ምርትን በምርምርና ፈጠራ በማገዝ የአየር ንብረት ለውጥን እንዲቋቋም ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አንስተው፤ አገራቱ በሚያመርቱት ምርት ላይ እሴት ከመጨመር ባሻገር በአስተሻሸግ ላይ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የጣሊያን የውጭ ጉዳይና ዓለምአቀፍ ትብብር ሚኒስቴር የልማት ትብብር ዳይሬክተር ጄነራል ስቲፋኖ ጋቲ እንደገለጹት፤ አገራቸው በተለይም ለኢትዮጵያና ለዩጋንዳ የቡና ምርትና ምርታማነት ድጋፍ እያደረገች ነው።

ቡና ለዓለም ኢኮኖሚ ያለውን ጠቀሜታ ግምት ውስጥ በማስገባት በዘርፉ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በትብብር መፍታት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

የፋኦ ዋና ዳይሬክተር ኩ ዶንግዩ እንደገለጹት፤ ቡና 80 በመቶ አነስተኛ ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮች መተዳደሪያ መሆኑን አንስተዋል።

በቡና ምርት ላይ የተሰማሩ የአነስተኛ ማሳ አርሶአደሮች ለአየር ንብረት ለውጥ ለዓለም የቡና ዋጋ መዋዠቅ፣ ከምርቱ ተገቢውን ጥቅም እንዳያገኙ ማድረጉንም አመልክተዋል።

ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የአገራት ትብብር ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

"የቡና እሴት ሰንሰለት ሽግግርን ማሳደግ''  በሚል ርዕስ የፓናል ውይይት የኢትዮጵያና ጣሊያን መንግስታት፣ የተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት፣ የዓለምአቀፉና የአፍሪካ የቡና ደርጅቶች በጋራ ያዘጋጁት ነው።

ምንጭ #ኢዜአ

Gallery

Gallery image 1
Gallery image 2
Gallery image 3
Gallery image 4
Gallery image 5
Gallery image 6

Tags

#ecta#coffee#farming#united nations#un