በካናዳው "Fraser Institute" የተዘጋጀው የ2024 ዓመታዊ የማዕድን ኩባንያዎች ጥናት፣ ኢትዮጵያ በማዕድን ኢንቨስትመንት ማራኪነት ደረጃ ከአለም መጨረሻ ላይ መቀመጧን አመላክቷል። ጥናቱ 82 ሀገራትን ገምግሞ ለኢንቨስትመንት ማራኪ የሚያደርጉ የፖሊሲ መረጋጋት እና ግልጽነት ላይ ችግሮች እንዳሉ በመጠቆም ኢትዮጵያን ከሁሉም በታች አስቀምጧታል። የኢንቨስትመንት ማራኪነት ደረጃው የሀገሪቱን የጂኦሎጂካል አቅም ከመንግስት የፖሊሲ ማዕቀፎች ጋር በማጣመር የሚሰላ ነው። ምንም እንኳን ኢትዮጵያ በሀብት የበለፀገች ብትሆንም፣ ደካማ የፖሊሲ አሰራር ኢንቨስተሮችን እያራቀ መሆኑን ጥናቱ ያሳያል።
ጥናቱ እንደ የግብር አወሳሰን፣ የህግ ስርዓት እና የፖለቲካ መረጋጋት ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮችን የሚገመግም ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በዚህ ምድብ ውስጥ ካሉ 10 ዝቅተኛ ደረጃ ከተሰጣቸው ሀገራት ውስጥ አንዷ ነች። የጥናቱ ተሳታፊዎች እንደገለጹት፣ የማዕድን ሀብት መሠረታዊ ቢሆንም፣ 40% ያህሉ የኢንቨስትመንት ውሳኔዎች የሚወሰኑት በፖሊሲ አሰራር ላይ ነው። ይህም ግልፅ ደንቦች፣ የፖለቲካ መረጋጋት እና ፍትሃዊ የህግ ማዕቀፎች የማዕድን ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ምን ያህል ወሳኝ እንደሆኑ ያመለክታል። ሪፖርቱ ኢትዮጵያ የፖሊሲ ክፍተቶቿን ካልሞላች፣ ኢንቨስትመንቶች ግልጽ እና ባለሀብት ወዳድ ወደሆኑ ሀገራት ሊዞሩ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል።