አዳዲስ የቡና ዝርያዎችን ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ቡና፣ ሻይና ቅመማ-ቅመም ባለስልጣን አስታወቀ
Back

አዳዲስ የቡና ዝርያዎችን ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ቡና፣ ሻይና ቅመማ-ቅመም ባለስልጣን አስታወቀ

ECTA
5 min read

ሀዋሳ: ነሐሴ 07/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አዳዲስ የቡና ዝርያዎችን ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ቡና፣ ሻይና ቅመማ-ቅመም ባለስልጣን አስታወቀ።

በክልሉ የቡና ዘር ዝግጅት ስራ ላይ ለባለሙያዎችና ለአርሶ-አደሮች የአሰልጣኞች ስልጠና የተሰጠ ሲሆን፥ የቡና ዘር አዘጋጆች የተሻሻሉ ዝርያዎችን እንዲያገኙ ቢደረግ የበለጠ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ተመላክቷል። 

ከቡና ዘር ዋጋ ዝቅተኛነት ጋር በተያያዘ የአርሶ-አደሮች ዘር የማዘጋጀት ተነሳሽነት እየቀነሰ መሆኑን ተናግረው፥ መፍትሔ የሚሻ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል። 

የቡና ዘር ዝግጅት ከፍተኛ ልፋት የሚጠይቅና ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ አርሶ-አደሩ ለልፋቱ በሚመጥን ዋጋ የሚሸጥበትን ገበያ ማመቻቸት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የቡና ዘር ዝግጅትና ጥራት ጉዳይ ከሀገር ኢኮኖሚ እድገት ጋር የሚያያዝና ትኩረት የሚሻ በመሆኑ ስልጠናውን ለሁሉም የቡና ዘርፍ ተዋንያን ማድረስ እንደሚገባ ተናግረዋል። 

ዘር አዘጋጆችን በማበራከት የሚከሰተውን የምርጥ ዘር እጥረት መቅረፍ እንደሚገባ ነው የተናገሩት። 

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቡና፣ ሻይና ቅመማ-ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አስራት መኩሪያ በስልጠናው የተሳተፉ አካላት የቡና ዘር የሚያዘጋጁ አርሶ-አደሮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ሁሉም ወረዳዎች ከደጋፊ አካላት ጋር በመተባበር  የአርሶ-አደሮችን ተጠቃሚነት ማሣደግ እንደሚችሉ አመላክተው ፤ በክልሉ አዳዲስ የቡና ዝርያዎችን ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 

የቡና ዘር አዘጋጅ አርሶ-አደሮችና ማህበራት የመደራደር አቅማቸውን በማሳደግና የሳይንሳዊ አሰራር ስርዓትን በሚያስፋፋ መንገድ እንዲሁም በሚዛናዊነት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል። 

የቡና ዘር ዋጋ አዘጋጅ አርሶ-አደሮችና ማህበራትን ተጠቃሚ በሚያደርግና የወቅቱን የገበያ ሁኔታ ከግምት ባስገባ መንገድ እንዲሆን በትብብር እንደሚሰራ ጠቁመዋል። 

የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተርና የልማትና ጥበቃ ዘርፍ ኃላፊ አቶ በላይ ኮጁአብ ክልሉ ከራሱ አልፎ ወደሌሎች አካባቢዎች በሚያሰራጨው ምርጥ ዘር ሀገርን መጥቀም ችሏል ብለዋል። 

አርሶ-አደሮች የልፋታቸውን ዋጋ እንዲያገኙ ለማድረግ ተባብሮ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረው ፤ በዘር አዘገጃጀት ላይ የሚስተዋሉ የጥራት ችግሮችን መቅረፍና የአዘጋጅ ማህበራትን አቅም ማሳደግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። 

ህገ-ወጥ የቡና ዘር ዝግጅት አርሶ-አደሮችንና  ዘርፉን እንዲሁም ሀገርን የሚጎዳ በመሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል። 

በመድረኩ የክልል፣ የዞኖች፣ የወረዳዎችና የቀበሌ የዘርፉ ባለሙያዎችና አርሶ-አደሮች ተሳትፈዋል።

Gallery

Gallery image 1
Gallery image 2
Gallery image 3
Gallery image 4
Gallery image 5
Gallery image 6

Tags

#ecta