ሐዋሳ
ከአውሮፖ ኅብረት ከደን ጭፍጨፋ ነጻ የቡና ምርት የሚያስገድደው ደንብ መስፈርት አሟልቶ ከመገኘት ጋር በተያያዘ የጂኦስፓሻል ዳታ አሰባሰብና የመረጃ ቋት አስተዳደር ላይ ከኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ እና አዲስ አበባ ለታደሙ የቡና አልሚዎች፣ አቅራቢዎችና ላኪዎች እንዲሁም የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የስራ ኃላፊዎችና ባለሞያዎች ስልጠና በሐዋሳ ከተማ በመሰጠት ላይ ይገኛል።
ስልጠናውን አቶ መስፍን ቃሬ የሲዳማ ክልል ቡናና ፍራፍሬ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር በንግግር ከፍተዋል። በንግግራቸውም ባሳለፍነው በጀት ዓመት 64 ሀገራት የኢትዮጵያን ቡና እንደገዙ ገልጸው በያዝነው በጀት ዓመት ደግሞ 84 መዳረሻዎች ይኖራሉ ተብሎ እንደሚታመን ገልጸዋል። ከዚህ ከ30 በመቶ በላይ የወጭ ቡናችንን የሚገዙት የአውሮፓ ኅብረት ነው ብለዋል። ኅብረቱ ደግሞ በቡናው ብቻ ሳይሆን ወደ ሰባት ምርቶች ደን የተመነጠረባቸው ከሆኑ ከ2017 ጥር ወር ጀምሮ ወደ አገራቸው እንዳይገቡ መመሪያ እንዳወጡ አስታውሰው በተደረገ ድርድር ጊዜ ገደቡ ለአንድ ዓመት ተራዝሞ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ይህ ቢሆንም እንደኢትዮጵያ ቡና ተመንጥሮ ቡና እሚተከልበት ስጋት እንደሌለ የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ ከዚህም አንጻር በአግሮፎሬስትሪ አካባቢ ያላቹ ሰልጣኞች እንደመሆናቹ መረጃውን ሰብስባቹ በመተንተን ለኅብረቱ እንዲደርስ ማድረግ ትኩረት ሊሰጡት የሚገባ ጉዳይ ነው ሲሉ አሳስበዋል።
ከዋና ዳይሬክተሩ ንግግር በኋላም ከአውሮፓው ደን አንጻር ልዩ ልዩ ስልጠናዎች ተሰጥተዋል። እነዚህም ቀጣይነት የጠበቀ የደን አስተዳደርና ለቡና ስነምኅዳር ያለው ጠቀሜታ፣ ለጂኦስፓሻል ዳታ አሰባሰብ ጠቀሜታ ላይ የሚውሉ መሳሪያዎችና መረጃ አሰባሰብ፣ መረጃ ማከማቸትና ማጥራትና እስከዛሬ ድረስ የተሰበሰቡ ሲንግል ፖይንት ዳታ ማጽደቅ ላይ የተቀሰሙ ትምህርቶች ላይ ስልጠናዎች የተሰጡ ሲሆን በቀጣይ ለጂኦስፓሻል መረጃ አሰባሰብ ጠቀሜታ ላይ የሚውሉ የተለያዩ የሞባይል አፕልኬሽን የትኞቹ እንደሆኑና እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ስልጠናዎች የሚሰጡ መሆኑን ከወጣው መርሀ ግብር ማወቅ ተችሏል።