በግብርናው ዘርፍ ውስጥ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን የመለየት ስራ መስራት እንዳለበት ባለሙያዎች አመላከቱ
Back

በግብርናው ዘርፍ ውስጥ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን የመለየት ስራ መስራት እንዳለበት ባለሙያዎች አመላከቱ

መነሃሪያ ሬዲዮ
5 min read

የብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት ከሰሞኑ ባካሄደዉ ምክክር በሃገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች መስተካከል ያለባቸውን እንዲሁም በጥሩ ጎን መቀጠል ያለባቸውን ነገሮች ያስቀመጠ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የግብርናው ዘርፍ አንዱ ነው ተብሏል፡፡ የግብርና ባለሙያው አቶ ደመላሽ ጉልማ፣ በሃገራችን በነበሩት 5 አመታት ውስጥ ከቀደመው ጊዜ የተሻለ የግብርና ምርታማነት እንዳለ አመላክተው በዛው ልክ የሚስተዋሉ በርካታ ክፍተቶች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ በቡና ምርታማነት፣ በአሳ እርባታ እንዲሁም በስንዴ ምርታማነት ላይ የታየው ንቅናቄ የምርቱ ውጤት የሚበረታታ መሆኑን የገለጹት ባለሙያው በተመሳሳይ በግጭት ምክንያት ለአመታት ያልተመረቱ በርካታ ሄክታር መሬት እንዳለም ገልጸዋል፡፡ የግብርና ግብዓቱና የሰላሙ ሁኔታ በአርሶአደሩ ዘንድ ትልቁ ተግዳሮቱ መሆኑን አቶ ደመላሽ አመላክተዋል፡፡ 

የግብዓት አቅርቦቱ የሁሉም አርሶአደር የሁልጊዜም ፈተና እንደሆነ ያመላከቱት ሌላኛዋ ገበሬና የግብርና ባለሙያዋ ወ/ሮ ክብርቴ አለማየሁ በሃገራችን የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ ጀምሮ እስከ ግብርና ሚንስቴር ድረስ የሚሰራው ስራ ዘመኑን የሚዋጅ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ በነበሩት 5 አመታት ውስጥ የተወሰኑ መሻሻሎች እንዳሉ ያመላከቱት ወ/ረ ክብርቴ፣ ግብርና ሚነስቴር በግብርናው ዘርፍ ውስጥ የሰራው ስራ በቂ እንዳልሆነና በዘርፉ ከሚሰማሩ ሰራተኞች ጀምሮ ጥብቅ የሆነ ጥናትና ክትትል ማድረግ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡ የአፈር ጥናት፣ የዘር ብዜት ምርምርና የባለሙያ ስልጠና ከመስጠት አኳያ የግብርና ሚንስቴር በዘርፉ ከፍተኛ የሆነ ስራን እንደሚጠበቅበትም አመላክተዋል፡፡ የግብርናውን ዘርፍ በሚፈለገው ልክ ለማሳደግ ግብርና ሚንስቴር እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም የራሳቸውን ድርሻ መወጣት እንደሚገባቸው ባለሙዎቹ አመላክተዋል፡፡

Tags

#farming#agriculture