በኢሉአባቦር ዞን ከ51 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡ ተገለፀ!
Back

በኢሉአባቦር ዞን ከ51 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡ ተገለፀ!

ECTA
5 min read

* "በነቀምቴ  ኢኒሼቲቭ" በቡና ላይ ከፍተኛ ስራዎች በመሰራት ላይ ይገኛሉ።

መቱ

(ነሃሴ 04/2017 ዓ.ም፡ ኢ/ቡ/ሻ/ባ)

በበጀት ዓመቱ በኢሉአባቦር ዞን ከ51 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡ ተገልጿል።

የኢሉአባቦር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ መሃመድ ጠሃ አባፊጣ እንደገለፁት በኦሮሚያ ግብርና ቢሮ በኩል ከለውጡ ወዲህ ባሉት ዓመታት እንደ ክልል የአርሶ አደሩን ህይወት እና ክልሉን ለመለወጥ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ብለዋል ።

ምክ/ዋና አስተዳዳሪው እንዳሉት በዋናነትም ከሚጠቀሰው አንዱ የግብርናው ዘርፍ ሲሆን አራት(4) ዓላማዎችን አቅፎ የያዘ ሲሆን እነሱም በአርሶ አደር ደረጃ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ፣ሰፊ የሆነ የስራ ዕድል መፍጠር ፣ከውጭ የሚገዙ የግብርና ምርቶችንና ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶችና ግብዓቶች መተካት እና የኤክስፖርት ምርቶችን በማሻሻል የውጭ ምንዛሪን ማግኘት ናቸው በማለት አብራርተዋል ።

የውጪ ምንዛሪን በማመንጨት ረገድ የአንበሳውን ድርሻ የያዘው ቡና ሲሆን ከአሁን በፊት በክልልም ሆነ በዞናችን በቡና ዙሪያ የተሰሩ ስራዎች ጥሩ ቢሆኑም ካለን አቅም አንፃር ተገቢው የሆነ ትኩረት ተሰጥቶት በሙሉ አቅም ለመስራት "የነቀምቴ ኢንሸየቲቭ" በማለት በቡና ላይ ከፍተኛ ስራዎች በመሰራቱ የቡናን ምርትና ምርታማነትን መጨመርና ቡናን በጥራት ማምረት ተችሏል ብለዋል - ምክትል አስተዳዳሪው።

አቶ መሃመድጠሀ አክለውም በዞኑ ከ300 ሺህ ሄ/ር በላይ አዲስ ቡና ተጎንድለውና ተነቅለው ምርት መስጠት የጀመሩና በተጨማሪ ከ400 ሺህ ሄክታር በላይ የጫካ ቡና በድምሩ ከ700 ሺህ ሄክታር በላይ የቡና ሽፋን በዞኑ የሚገኝ ሲሆን ከ51 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል ብለዋል ።

አቶ መሃመድጠሀ የቡና ዋጋ ከፍተኛ መሆኑን ከተሰማበት ከ47 ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዘንድሮ ይፋ ያደረገው 2.653 ቢሊዮን ዶላር ሀገራችን ገቢ ማድረግ የቻለችና የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት በተጨባጭ ያረጋገጥንበት ወቅት በመሆኑ ስራችን አጠናክረን ልንሰራ ይገባል ብለዋል ።

በመጨረሻም በገለፃቸው በኢሉአባቦር ዞን ከማህበራዊ ፋይዳው አንፃር ሲታይ  ቡና እና የዞኑን አርሶ አደርም ሆነ የከተማውን ነዋሪ ማለያየት እንደማይቻል ገልፀው ከ65% በላይ የዞኑ ነዋሪ ህብረተሰብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኑሮው የተሳሰረው በቡና በመሆኑ "ስንኖር በቡና- ስንሞትም በቡና"  በሚል አባባል በደስታ እና በችግር ጊዜ ከቡና ጋር ያለውን ትስስር ይገልፃል በማለት አብራርተዋል ።

ለቀጣይ በጀት ዓመትም ከፍተኛ የቡና ንቅናቄ በመፍጠር የበለጠ ለመስራት እንደታቀደ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ቡድን በቦታው ተገኝቶ ዘግቧል።

Gallery

Gallery image 1
Gallery image 2
Gallery image 3
Gallery image 4
Gallery image 5
Gallery image 6

Tags

#ecta#illibabur