አዲስ አበባ
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ያዘጋጀው እና ክቡር ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አዱኛ ደበላ እንዲሁም ምክትላቸው ክቡር አቶ ሻፊ ዑመር የተገኙበት በበጀት ዓመቱ ዝርዝር ዕቅድ እና በ2017 ዕቅድ አፈጻጸም ዙሪያ እንዲሁም መንግስት ባስቀመጠው የልማትና የብልጽግና ስትራቴጂና አቅጣጫ ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል ፡፡
ከመቶ በላይ የሚሆኑ የቡና ላኪዎች አቅራቢዎችና አልሚዎች ተገኝተዋል።
የቡናው ባለሃብት ወቅቱ የሚጠይቀውን የልማት እና የለውጥ እንቅስቃሴ በመደገፍ ማህበራዊ ግደታቸውን እየተወጣ መንግስት የያዘውን ቁርጠኛ የእድገትና የልማት ጉዞ እንዲደግፍ እና የሚጠበቅበትን ግዴታ እንዲወጣ በሚል ሰነድ የቀረበ ሲሆን፤ የመወያያ ሰነዱን ያቀረቡት ክቡር አቶ ሻፊ ኡመር በኢቡሻ ባለስልጣን ምክ/ዋና ዳ/ር እና የግብይት ዘርፍ ሀላፊ ናቸው ፡፡
ሰነዱ ቀርቦ ውይይት ከተካሄደ በኋላ ክቡር ዶክተር አዱኛ ደበላ የኢቡሻ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር እንዳሉት ‹‹መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫና ከግብርና ሚኒስቴር በተላከ የማስፈጸሚያ ሰነድ መሰረት በኢትዮጵያ በተመረጡ ሁለት ከተሞች እና ክልሎች/ቤኒንሻጉል ጉሙዝ እና ሸገር ከተማ በሚለሙና በሚሰሩ የከተማና ኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ለሚያስፈልገው የፋይናንስ ወጭና የግንባታ ቁሳቁስ ፍላጎት እንዲሁም የተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ የቡናው ባለሃብት ከ225 ሚሊየን ብር በላይ በማዋጣትና የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ በልማቱና ዜጎችን በማገዝ የራሱን አሻራ ማኖር ይገባል›› ብለዋል ፡፡
የቡና ባለሃብቱ እና ተወካዮቸው በሰነዱ ላይ በተወያዩበትና አስተያየት በሰጡበት ወቅት የመንግስትን አቅጣጫ በመቀበል የሚጠበቅባቸውን መብትና ግዴታ በመወጣት ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙና ልማቱን እንደሚደግፉ በደስታ ገልጸው፣ መንግሰትና የኢ/ቡ/ሻ ባለስልጣን ሃላፊዎችም የቡናውን ባለሃብት ከባንክ ቤት ጋር ያለውን ቢሮክራሲና ነጋዴው በወቅቱ ቡናን ለውጭ ገበያ እንዲያደርስ የሎጂስቲክና የመጋዘን ችግሮችን ለመፍታት እንደጠበቃና የቅርብ አጋር ሆናችሁ እንድታግዙን ብለዋል ፡፡ ክቡር ዶ/ር አዱኛ ከባለሃብቱ የተነሱ ጥያቄዎችንና ሃሳቦችን ተቀብለው ለተነሱ ችግሮች አፋጣኝ መልስ እንደሚሰጧቸው ገልጠው በተለይ ውድድር በበዛበት ገበያ ወስጥ ሆናችሁ ባሳለፍነው አመት ውጤታማ ስራ ብትሰሩም የአለም ገበያ ባለበት የሚቀጥል ባለመሆኑ በተለይ የአውሮፓ ህብረት ያወጣውን የኢዩዲአር መመሪያ በማክበር የኢትዮጵያ ቡናን በአውሮፓ ገበያና በሌሎችም ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ የጂኦ ሎኬሽን የቡና መሬት መረጃ የአምራቹን የባለቤትነት እና ቦታውን የያዘ ሰርተፊኬት መረጃ ወደኛ በማቅረብ ታማኝ መረጃ ለአውሮፓ ህብረት እንድናቀርብና ህጋዊ ገበያ ተከትላችሁ የላቀ ገቢ ለናንተም ለሃገራችሁም እንድታመጡ አሳስባለሁ ብለዋል ፡፡
በመጨረሻ አቶ ሻፊ ኡመር በተለይ ከዛሬ የነገው የአለም ቡና ገበያ ሊወደድ ይችላል በሚል የተሳሳተ ሃሳብ ቡናን በመያዝና ከመጋዘን በማስቀመጥ ቡና ወደ ወቅታዊ ገበያ እንዳይወጣና እንዳይቀርብ የሚደርጉ አንዳንድ የቡና ባለሃብት ወይም አቅራቢዎች ሃገርንም ራሳቸውንም ኪሳራ ላይ እንዳይጥሉ አሁን ባለው አጋጣሚ እና መልካም ገበያ እንዲጠቀሙ አደራ እላለሁ ብለዋል ፡፡
ከውይይቱ በኋላም ለተመዘገበው ውጤት የኬክ ቆረሳ የተካሄደ ሲሆን እድሳቱ የተጠናቀቀውን የባለሥልጣኑን ህንፃ ተዘዋውረው ተጎብኝቷል።