የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የስርዓተ ጾታና አየር ንብረት ላይ በተዘጋጀ የትግበራ ዕቅድ ላይ የተለያዩ ባለድርሻና አጋር አካላትን በመጋበዝ ውይይት አካሂዷል፡፡ በውይይቱም ባለስልጣኑን ጨምሮ የሲቪል ማኅበራት ድርጅት፣ የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የምርምር ተቋማት ተሳትፈውበታል፡፡
የውይይቱን መድረክ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሠፊሳ አባቡ በንግግር ከፍተዋል፡፡ በንግግራቸውም የተዘጋጀው ሰነድ ጥናትን መሠረት ባደረገ መልኩ የተዘጋጀ እንደሆነና ዓለማቀፍ የስርዓተ ጾታና የአየር ንብረት ነባራዊ ሁኔታዎችን በዳሰሰ መልኩ እንደተዘጋጀ ገልጸዋል፡፡ ሰነዱ ቢዘጋጅም ለተግባራዊነቱ በቂ ዝግጅት ማድረግ ስለሚገባ ለዕቅዱ ተግባራዊነት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለማግኘት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የተለያዩ አካላት ጋር ውይይት ለማድረግ መድረኩ እንደተጠራ ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ለታቀደው እቅድ በተፈለገው መጠን፣ ጥራትና ጊዜ መተግበር የተለያዩ የሚመለከታቸው ፕሮጀክቶች ትብብር እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል፡፡ የስርዓተ ጾታና አየር ንብረት ሁኔታ ለባለስልጣን መስሪያቤቱ ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ ገልጸው በዚህም መሠረት ባለስልጣኑ ለዕቅዱ መፈጸም ስኬት እንደሚተጋ ተናግረዋል፡፡ በስተመጨረሻም የታዳሚው በተለይ የሴቶች ንቁ ተሳትፎ እንዲኖር አሳስበዋል፡፡
ዕቅዱን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢኒስቲትዩት የስርዓተ ጾታና እንክብካቤ ተመራማሪ የሆኑት ወ/ሮ ለምለም አበበ አቅርበዋል፡፡ በመንደርደሪያቸውም ዕቅዱ ጥናትን መሠረት ባደረገ መልኩ የተዘጋጀ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የተዘጋጀው ሰነድ ግቦችና ዓላማዎችን ሲገልጹም የጾታ እኩልነትን፣ የአየር ንብረት መላመድ፣ የረጅም ጊዜ የከባቢያዊ ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ቀጣይነትን በማሻሻል የኢትዮጵያ የቡና ሴክተር ችግሮችን ተቋቋሞ የማለፍ አቅምን የማጎልበት ግብን ያነገበ እንደሆነ ካቀረቡት ሰነድ ማወቅ ተችሏል፡፡ ዝርዝር ዓላማውንም ሲያቀርቡ ከጾታ እኩልነት፣ ከአየር ንብረት መቋቋም፣ ከአቅም ግንባታ፣ ከእሴት ሰንሰለት ልማት፣ ከኑሮ ገቢ ልማት፣ ከተቋማት መጠናከር ጋር በተያየዘ በርካታ ዝርዝር ዓላማዎች እንዳሉት አስረድተዋል፡፡
በቦታው ተገኝተን እንደተገነዘብነውም ዕቅዱ በይዘት የጾታ ሃላፊነት መወጣት አቅም ማዳበር፣ አየር ንብረትን የሚቋቋሙ የግብርና ልምዶች፣ የሀብትና አገልግሎት ተደራሽነት ማሳደግ፣ የፋይናንስ አገልግሎት አካታችነት ማሻሻል፣ የኤክስቴንሽን አገልግሎት ተደራሽነት፣ የቡና ልማት፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ተቋማትን ማጠናከርና የፖሊሲ ሁኔታ፣ ምርምሮችን ማካሄድና ዕውቀት ማዳበር፣ ማኅበረሰብን መሠረት ያደረገ የዕለት ገቢና ችግሮችን ተቋቁሞ ማለፍ ላይ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት፣ የአየር ንብረት መረጃና ቅድመ መከላከል ማስጠንቀቂያ ስርዓቶች፣የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ትብብር እና የዕውቀት ሽግግር፣ ቁጥጥር ክትትል እና የመማማር ማዕቀፈ ማዘጋጀት፣ የሚጠበቁ ውጤቶች፣ ለተፈጻሚነቱ ባለድርሻ አካላቱ እነማን እንደሆኑና ሚናቸው፣ ለዕቅዱ መፈጸም የሚጠይቀው ወጪ ያካተተ እንደሆነ ለመረዳት ችለናል፡፡
የትግበራ ዕቅዱ ከቀረበም በኋላ በቡድን ውይይት ሀሳቦች መንጭተው ውይይት ተካሂዶባቸው የመድረኩ ፍጻሜ ሆኗል፡፡
ዕቅዱ በስፓኒሽ ኮኦፐሬሽን የገንዘብ ድጋፍ ኦስሪያ በተባለ ድርጅት ለቡናና ሻይ ባለስልጣን ግብአትነት የተዘጋጀ እንደሆነ ከመድረኩ አዘጋጅ ክፍል ለማወቅ ተችሏል፡