በተለይ ለአርሶ አደሩ በስፋት ተደራሽ እንደሚሆን የተገለጸው ለወገን አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም በይፋ ስራ ማስጀመሩን ሐምሌ 27 ቀን 2017 ዓ.ም አስታውቋል። ተቋሙ የብድርና የፋይናንስ ተቋም ሆኖ ከተመሰረተ ሶስት አመታት ቢያስቆጥርም በተለያየ ምክንያት ወደ ስራ አለመግባቱንና ከባለፈው ሰኔ ወር ጀምሮ ግን ስራ ስለመጀመሩ ያለወገን አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አስናቀ ሃይለ ሚካኤል ተናግረዋል። ለወገን ማይከሮ ፋይናንስ የተመሰረተው 39.3 ሚሊዮን ብር የተፈረመ እና 10.3 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል በማስመዝገብ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የተከፈለ ካፒታል 21.6 ሚሊዮን ብር ደርሷል ተብሏል።
በ27 ባለ አክሲዮኖች የተቋቋመው የፋይናንስ ተቋሙ እስከ መጪው ነሐሴ ወር መጨረሻ ድረስ 40 ሚሊዬን የተከፈለ ካፒታል ይኖረዋል ሲሉም ዋና ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል። ከመስከረም ወር 2018 ዓ.ም ጀምሮ ከ100 እስከ 200 ሚሊዬን አዳዲስ አክሲዮኖችን ወደ ገበያው እንደሚያስገቡም ገልጸዋል። የፋይናንስ ተቋሙ በዋናነት በሁለት ዘርፎች ላይ አገልግሎት ይሰጣል ያሉት አቶ አስናቀ አንደኛው በገጠር ለሚገኙ አርሶ አደሮች ሲሆኑ ሁለተኛው ደግሞ በከተማ ውስጥ አነስተኛ የትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰጡ አካላት መሆኑንም ተናግረዋል። ተቋሙ እንደማንኛውም የብድርና የፋይናንስ ተቋም ከማበደር በዘለለ በተለይ አርሶ አደሩ በቀላሉ ባለ አክሲዮን የሚሆንበትን አማራጭ እንደሚያሰፋ እና በተመሳሳይ ለአነስተኛ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችም አገልግሎት እንደሚሰጡና በዘርፉ ከሚገኙ ፌደሬሽኖች ጋር ስምምነት ፈጽመው በጋራ እየስሩ ስለመሆናቸውም ዋና ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።