ለቡና ምርትና ምርታማነት እንዲሁም ጥራት መረጋገጥ ከቡና ዘር ዝግጅት ጀምሮ እስከ ግብይት ድረስ በልዩ ትኩረት መሥራት ያስፈልጋል፦አቶ ማስረሻ በላቸው
Back

ለቡና ምርትና ምርታማነት እንዲሁም ጥራት መረጋገጥ ከቡና ዘር ዝግጅት ጀምሮ እስከ ግብይት ድረስ በልዩ ትኩረት መሥራት ያስፈልጋል፦አቶ ማስረሻ በላቸው

ECTA
5 min read

በሸካ ዞን የ2018 ምርት ዘመን የቡና ምርት ዝግጅትና የጥራት ቁጥጥርን በተመለከተ ከክልልና ከዞን ባለድርሻ አካላት ጋር በቴፒ ከተማ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ይገኛል። 

በመድረኩ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው የቡና ምርት ለክልሉና ለሀገርቱ ኢኮኖሚ እድገት ያለው አስተዋጽኦ ወሳኝ በመሆኑ ምርታችንን ከፍ ለማድረግ የሚያስችሉ አዳዲስ ቴክኒኮችን በመጠቀም እና የጥራት ደረጃችንን በማሻሻል በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ መሆን አለብን ሲሉ ገልፀዋል።

ለቡና ምርትና ምርታማነት እንዲሁም ጥራት መረጋገጥ ከቡና ዘር ዝግጅት ጀምሮ በልዩ ትኩረት መሥራት እና በዘርፉ የሚስተዋሉ ውስንነቶችን መቅረፍ እንደሚገባም አሳስበዋል አቶ ማስረሻ።

የክልሉን የቡና ምርትና ምርታማነት አቅም ሙሉ በሙሉ በመጠቀም የቡናን ምርት በጥራትና በብዛት ማሳደግና ለገበያ ምቹ እንዲሆን ማድረግ ይገባል ያሉት አቶ ማስረሻ የቡና ጥራትና ብዛት ለማሳደግ ያረጁ ቡናዎችን መንቀል ፣የጥራት ቁጥጥር ፤የምርጥ ዘር ዝግጅት እና በቡና ህገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ዙሪያ መስራት ይገባል ሲሉ በአፅንኦት አንስተዋል።

የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ በወቅቱ እንደተናገሩት ዞኑ በቡናና በሌሎች ቅመማቅመም ምርት የሚታወቅ መሆኑን ጠቁመው የቡና ምርትን ከሚሰበሰብበት ጀምሮ እስከ መሸጫ ቦታ ድረስ ያለውን የጥራት ቁጥጥር ስርዓት ማጠናከርና ለገበያ ምቹ እንዲሆን ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ይህ ውይይት የዞኑን የቡና ምርት ጥራት ማሳደግ፣ የአቅርቦት ማነስ ችግሮችን መፍታት እና የቡና ህገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ቁጥጥር ብሎም በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

የሸካ ዞን ግብርና ደን አካባቢ ጥበቃና ህብረት ሥራ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አዕምሮ ደሳለኝ በዞኑ 87 ሺ ሄክታር የቡና ማሳ ሽፋን መኖሩን ገልፀው ከዚህ ውስጥ 67 ሺ ሄክታር ምርት እንደሚሰጥ ገልፀዋል።

በዚህ የውይይት መድረክ የቡና ምርትን ከችግኝ ዝግጅት እስከ ሽኝት ድረስ ያለውን የጥራት ሂደት የሚመለከቱ ጉዳዮች፣ የዘርፉ ተዋንያን የሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶችና በቀጣይ የዘርፉ ውጤታማነት ዙሪያ ሰፊ ውይይት ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።

የሸካ ዞን ግብርና ደን አካባቢ ጥበቃና ህብረት ሥራ ልማት  መምሪያ የቡና ሻይና ቅመማቅመም ዘርፍ ኃላፊ አቶ አዳምሰገድ ኃይሌየሱስ የመወያያ ሰነድ እያቀረቡ ይገኛሉ።

በውይይቱ ላይ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል  ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው፣ የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮች፣የከተማና የወረዳ አመራሮች፣የግብርና ባለሙያዎች፣የልማት ድርጅቶች ተወካዮች፣ የቡና አርሶ አደሮች ተወካዮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

Gallery

Gallery image 1
Gallery image 2
Gallery image 3
Gallery image 4
Gallery image 5
Gallery image 6

Tags

#ecta#coffee