አዲስ አበባ
የገንዘብ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ጋር በመተባበር የአውሮፓ ህብረት ወደ አባል አገራቱ የሚገባውን የቡና ምርት በተመለከተ በቅርቡ ተግባራዊ የሚደረገው ከደን ጭፍጨፋ ነጻ ደንብ (EUDR) መስፈርቶችን በማሟላት ረገድ አገራችን እያከናወነች ያለችውን ተግባራት እና ጥረት ለመገምገም፣ ያለችበትን ደረጃ ለማየት እና የሄደችበትን ርቀት በተመለከተ ለመምከር ወሳኝ የሆነ ስብሰባ ተካሂዷል።
በስብሰባው ላይ ከGIZ፣ ከጀርመን ኤምባሲ እና ከUNDP የተውጣጡ ተሳታፊዎችን ጨምሮ የመንግስት ተቋማት፣ የልማት አጋሮች፣ የቡና አ/አደር እና አልሚዎች፣ ህብረት ስራ ማህበራት እና ዩኒየኖች፣ ላኪዎች እና የቡና ገዥ ማህበራት ተወካዮች ተገኝተዋል።
ክብርት ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ እንዳሉት ቡና ለአገሪቱ ወሳኝ ሴክተር ከመሆኑ ሌላ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ሚና ከመወጣት ባለፈ ዓለም አቀፍ የዘላቂነት ደረጃዎችን የሚያሟላ የቡና አቅርቦት ሰንሰለት ለመገንባት ያለውንም ሚና በዝርዝር አስረድተዋል። መንግስትም ይህን ዘርፍ ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት እና ከአጋር አካላት ጎን በመሆን ወደ ላቀ ደረጃ መድረስ እንዲችል አስፈላጊውን ሁሉ እገዛ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ በቡና አቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ ጠንካራ የጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ መረጃ/Geo spacial location Data የመከታተያ እና የመተዳደሪያ ስርዓትን በመዘርጋት በኩል ቀድሞ መሄድ የተቻለበት ሁኔታ እንዳለ በውይይቱ ወቅት የተገለፀ ሲሆን ቡናን ከማሳ ጀምሮ እስከ ኤክስፖርት ሰንሰለቱ ድረስ መከታተል የሚያስችል አንድ ሀገር አቀፍ ፕላት ፎርም መቋቋሙ እና ወደ ስራ መግባቱ በውይይቱ ወቅት ተነስቷል።።
ቀሪ ሊሰሩ በሚገቡ ጉዳዮች ዙሪያ እንዲሁም ሊከሰቱ በሚችሉ ተግዳሮቶችንም በምን ሁኔታ መፍታት እንደሚቻል፣ ያሉ ተነሳሽነቶች ተጠናክረው የሚችሉበትም መንገድ መድረኩ በስፋት ካነሳቸው እና ከተወያየባቸው ጉዳዮች መካከል ይገኙበታል።
የፌዴራል ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አዱኛ ደበላ እንዳሉት EUDR ህብረቱ በሚጠይቀው መስፈርት እና በተቀመጡ ደንብ እና የህግ አግባቦች መሠረት ተግባራዊ እንዲሆን ለማድረግ ሰፊ ርቀቶች የተሄደበት መሆኑን ገልፀው፤ በዚህ ረገድ አገሪቱ በአውሮፓ ያላትን የገበያ ድርሻ እንዳታጣ እና ይልቁንም አጠናክራ እንድትቀጥል ለማድረግ እንደ መንግስት በርካታ ስራዎች መሠራታቸውን እና ወደፊትም ዘርፉ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግ መንግስት ያለውን ጠንካራ ቁርጠኝነት አፅንዖት ሰጥተው አስረድተዋል።
ክቡር ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም በባለስልጣን መ/ቤቱ በኩል አንድ ብሄራዊ ስርዓት ባለው መረጃ ቋት ውስጥ ሁሉንም የተሰበሰቡ የጂኦግራፊያዊ አካባቢ መረጃዎችን ማእከላዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ ቡናና ሻይ ለማህበራት እና ለክልሎች ተግባራዊ ስለሚሆንበት ሁኔታ አቅጣጫ እንደሚሰጥም አስታውቀዋል።
ይህ አካሄድም አንድ ወጥ፣ አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ ይፈጥራል፣ የመረጃ መዛባትን ያስወግዳል።፤ ለላኪዎች፣ ለገዢዎች እና ለዘርፉ አካላት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራልም ነው ያሉት ክቡር ዶ/ር አዱኛ።
የ EUDR ተግባራዊነት ቀነ-ገደብ በፍጥነት እየቀረበ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ስብሰባው እነዚህን ውጥኖች በብቃት እና በቁርጠኝነት መተግበር ስለሚቻልበት ሁኔታም በስፋት መክሯል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ የቡና ዘርፍ የEUDR መስፈርቶችን ከማሟላት ባለፈ በዓለም ገበያ እንዲበለፅግ የልማት ኤጀንሲዎችን ጨምሮ የሁሉም አጋር አካላት ድጋፍ ማሳደግ እንደሚገባ መግባባት ላይ ተደርሷል። ሁሉም ተሳታፊዎችም ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ታዛዥነትን እንድታገኝ ጥረታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ በመዝጊያው ላይ የኢትዮጵያ እና አውሮፓን ጠንካራ የቡና ንግድ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር በ 2025 መጨረሻ ላይ የ EUDR ተገዢነት ቀነ-ገደብ ማሟላት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል.
እስካሁን በባለድርሻ አካላት መካከል የነበረው የትብብር መንፈስ እና ጠንካራ ስርዓቶች የቀለጠ ሊጎለብቱ እንደሚችሉ ያላቸውንም ተስፋ ገልጸዋል።