የሲዳማ ክልል አለታ ወንዶ ወረዳ ቨርም ኮምፖስት የልማት ስራ ተጎበኘ።
ኅዳር 29/2018 ዓ.ም
አለታ ወንዶ
በተከበሩ አቶ ሰለሞን ላሌ የተመራ የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት እና የተለያዩ ክልሎች አመራሮችና ባለሞያዎች የሲዳማ ክልል አለታ ወንዶ ወረዳ የቨርሚ ኮምፖስት የማምረት ስራን ጎብኝተዋል። ተሞክሮን የማጋራትና የማስፋፋት ግብን ባነገበ መልኩ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ነበር የጉብኝት መርሀ ግብሩን ያዘጋጀው።
በቅኝቱም ወቅት ስለአለታ ወንዶ ኮምፖስት ዝግጅት ገለጻ አድርገዋል።
በገለጻቸውም 17 ኢንዱስትሪ እንዳሉ ገልጸው የምርት ስርዓት ሆኖ እያንዳንዱ አቅራቢ ቨርሚ ኮምፖስት የማዘጋጀትና ለአርሷደሩ የማከፋፈል ግዴታ አለበት ብለዋል። በዚህም ሁሉም ሳይቶች ማለትም የግልም የማኅበርም ቨርም ኮምፖስት ማዘጋጀት መሟላት ያለባቸው አንዱ መስፈርት ነው ብለዋል። ትስስርም ተፈጥሮ እያንዳንዱ ኢንዱስትሪ ኮምፖስት አምርቶ ቡና ለሚያቀርቡለት አርሷደሮች የሚያቀርብ ሲሆን ማኅበራቱ ደግሞ ለአባላቶቻቸው ያቀርባሉ ሲሉ ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪዎቹ የቨርም ኮምፖስት ስራም ሰምሮ ምርትና ምርታማነት አድጎ በቡና ምርት ረገድ የተጎበኘው ሳይት 1.7 ሚሊየን ኪ.ግ ቡና ለመሰብሰብ እንዳቀደና እስካሁን ድረስ 800 ሺ ኪሎግራም እንደሰበሰበ ተገልጿል።
ከአለታ ወንዶ የሸርሚ ኮምፖስት አዘገጃጀት ቅኝት በኋላም ወደ ሐዋሳ በመመለስ ውይይት ተካሂዷል። በውይይት መርሀ ግብሩም መሠረት ክቡር አቶ መስፍን ቃሬ የሲዳማ ክልል ቡና ቅመማ ቅመምና ፍራፍሬ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አጠቃላይ ስለክልሉ የቨርሚ ኮምፖስት ዝግጅት አፈጻጸም አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል። በገለጻቸውም ክልላቸው 2017 በጀት ዓመት ላይ ቡናን በመደበኛ ኮምፖስት ማምረት አንችልም ብለው በመነሳት ቨርሚ ኮምፖስት ላይ ትኩረት አድርገው እንደሰሩ ተናግረዋል። ይህ ጥረት እስከፍጻሜው ይደርስ ዘንድም አስፈጻሚ አካላትን በመያዝ ሰፊ የንቅናቄ ስራ ተሰርቷል ብለዋል። ይህም ሰምሮ አንደ ወረዳ ቢቾ ቀበሌ ላይ እንዳሉት እንደ አየለ በቸራ ያሉ አርሷደሮች እስከ 19 ኩንታል በሄክታር እስከማምረት የደረሱ አርሷደሮችም አሉ ሲሉ ገልጸዋል።
ወደ 172 ኢንዱስትሪዎች ወደስራ እንዲገቡ ዕቅድ ተይዞ 139 ወደ ስራ ገብተዋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ከዚህም አልፎ እያንዳንዱ አርሷደር የራሱን ኮምፖስት እንዲያዘጋጅ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆ አውስተዋል። በዚህም የቡና ምርታማነት ከማሳደግ ባሻገር አንድ ኩንታል እስከ 1600 ብር እየተሸጠ በመሆኑ እንደአንድ የገቢ ምንጭ ሆኖ ይገኛል ሲሉ አክለዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ሰነድ ካቀረቡም በኋላ ከግብርና ቋሚ ኮሚቴ አባላትና ከክልሎች አመራሮችና ባለሞያዎች ሀሳብ ተሰንዝሮ ሰፊ ውይይት ተካሂዶ መርሀ ግብሩ ተጠናቋል።
ተከታታዮቻችን የዚህ መርሀግብር አካል የሆነ የቀርጫንሼ የቡና ልማት እንቅስቃሴ በባለፈው የዜና እወጃችን ያስነበብን መሆኑ ይታወሳል።
አሸናፊ ጌታሁን ከቦታው ዘግቦታል።








