የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ክቡር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) የሪፎርም ሥራዎችን አፈጻጸም ገመገሙ።
ሚያዝያ 10 ቀን 2018 ዓ.ም (አዲስ አበባ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ክቡር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና በተጠሪ ተቋማት እየተከናወኑ ያሉ የንግድ ዘርፍ የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ሥራዎችን ከአብይ ኮሚቴ አባላት ጋር በጥልቀት ገምግመዋል።
በግምገማ መድረኩ በንዑሳን ኮሚቴዎች የተከናወኑ ተግባራት በዝርዝር የቀረቡ ሲሆን፤ ክቡር ሚኒስትሩ ሪፎርሙን ተከትሎ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በአሠራር ግልጽነትና ተቋማዊ አቅምን በመገንባት ረገድ የተመዘገቡ አበረታች ለውጦችን ገምግመዋል። በተለይም አሠራሮችን ወደ ዲጂታል በማሸጋገር የንግዱን ማኅበረሰብ እንግልት የሚቀንሱ ውጤቶች መገኘታቸውን አረጋግጠዋል።
ክቡር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በቀጣይ ይበልጥ መሻሻል በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ የሥራ መመሪያ የሰጡ ሲሆን፤ ተቋማዊ ሪፎርሙ የንግድ ሥርዓቱን ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና ተወዳዳሪ ከማድረግ አኳያ ወሳኝ ሚና እንዳለው አጽንዖት ሰጥተዋል። የጀመርነውን የለውጥ ሥራ ከዳር ለማድረስና ለዜጎች ፈጣንና ምላሽ ሰጪ የሆነ የፐብሊክ ሰርቪስ አሠራርን በተቋሞቻችን ውስጥ ዘላቂ ለማድረግ በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየሠራን እንገኛለን ሲሉም ክቡር ሚኒስትሩ ገልጸዋል።








