ባለፉት ዘጠኝ ወራት በንግድ ሴክተሩ ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል።
( ሚያዝያ 08 ቀን 2018 ዓ.ም ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የ2018 በጀት ዓመት የ9 ወራት የሴክተር አፈጻጸም ግምገማን “ተወዳዳሪ ንግድ ስርዓትና የተሳለጠ የገበያ ትስስር ለኢኮኖሚያዊ ሽግግር!” በሚል መሪ ቃል ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና ከተጠሪ ተቋማት አመራሮች ጋር ማካሄድ ጀምሯል።
የግምገማ መድረኩን በንግግር የከፈቱት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ክቡር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በንግድ ሴክተሩ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር እጅግ የላቀ ውጤት ተመዝግቧል።
በተለይም በወጪ ንግድ ዘርፍ 7 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በማስገኘት የታቀደውን 121 በመቶ ማሳካት መቻሉ ትልቅ ስኬት መሆኑን ጠቁመዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ 2,936,270 የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎቶችን በመስጠት የእቅዱን109 በመቶ ማሳካት ተችሏል፡፡ ይህም ከፍተኛ ውጤት የዘርፉን አዳጊነት የሚያሳይ ሲሆን፤በተካሄዱ 1.5 መሊዮን የድህረ-ፈቃድ ኢንስፔክሽን ሰራዎች የጥፋት ደረጃዎች እየቀነሱ መጥተዋል።
የግብይት መሠረተ ልማትን በማስፋፋት የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ቁጥር 2190 መድረሱ ን እና በኢ-ኮሜርስ ዘርፍም ተጨባጭ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ቀደም ሲል በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጪ ወደ ውጭ ሀገር ተልከው ይመረመሩ የነበሩ ምርቶች፣ አሁን በሀገር ውስጥ ላቦራቶሪዎች እንዲመረመሩ በማድረግ ትልቅ ስኬት መመዝገቡን ጠቁመዋል።
የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከላትን በማበራከትና በማጠናከር ረገድ ሰፊ ውጤት መገኘቱንና በርካታ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ወደ ሥራ መግባታቸውን አብራርተዋል።






