የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ክቡር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና የተጠሪ ተቋማት የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም አፈጻጸም ገመገሙ።
(አዲስ አበባ፣ መጋቢት 05 ቀን 2018 ዓ.ም) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ክቡር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት በመገኘት፣ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና በተጠሪ ተቋማት እየተተገበረ ያለውን የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ሳምንታዊ አፈጻጸም ገምግመዋል።
በግምገማ መድረኩ ላይ እንደተመለከተው፣ በሪፎርሙ የዝግጅት ምዕራፍ የተቋቋሙ ሁሉም ኮሚቴዎች ያከናወኗቸው ተግባራት ውጤታማና አበረታች መሻሻል እያሳዩ መሆኑ ተረጋግጧል። በተለይም የተቋሙን አገልግሎት አሰጣጥ ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ የታለሙ ተግባራት በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ተመላክቷል።
ክቡር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ የሪፎርሙ ዋና ግብ ተቋማችንን በሰው ኃይል፣ በዘመነ አሠራርና በቴክኖሎጂ በመገንባት ቀልጣፋ፣ ተደራሽና ግልጽነት የሰፈነበት አገልግሎት ለዜጎችና ለንግዱ ማህበረሰብ መስጠት ነው። አክለውም ትላንት በነበረው ዝግተኛ አሠራር ዛሬንና ነገን መምራት ስለማይቻል፣ አሠራርንና አስተሳሰብን ከዘመኑ ጋር የማጣጣም ሥራችንን በቁርጠኝነት እንቀጥላለን ብለዋል።
ይህ የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም በዋናነት የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቶችን በማዘመን እንግልትን መቀነስ፤ ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም አገልግሎትን ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ማድረግ፤ የሰው ኃይል አቅምንና የሥራ ተነሳሽነትን ማሳደግ፤ በተቋማቱ ውስጥ ተጠያቂነትንና ግልጽነትን ማስፈን ላይ ትኩረት አድርጎ እየተከናወነ ይገኛል።









