የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ክቡር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) የነዳጅ ምርት በተገቢው መንገድ ቁጥጥር ተደርጎበት እንዲሰራጭና አገልግሎት ላይ እንዲውል የሕግ ማዕቀፍ ተዘገጅቶለት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ክቡር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በአዳማ ከተማ በተዘጋጀው የነዳጅ ግብይት ባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ላይ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሃገራችን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ፖሊሲን በመተግበር፣ የታዳሽ ኃይል አማራጮቻችን በማስፋትና የተፈጥሮ ጸጋችንን ተጠቅመን በኢነርጂ ራስን የመቻል ግባችንን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሜጋ ፕሮጄክቶችን በማከናወን ላይ መሆኗን ሚኒስትሩ አውስተዋል።
የነዳጅ ኃይል አስተዳደርና አቅርቦትም በዘላቂነት ልንከተለው የሚገባውን የኃይል አጠቃቀምና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ማረጋገጥን ታሳቢ ያደረገ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ይህ ስትራቴጂክ ምርት በተገቢው መንገድ ቁጥጥር ተደርጎበት እንዲሰራጭና አገልግሎት ላይ እንዲውል የሕግ ማዕቀፍ ተዘገጅቶለት በትግበራ ላይ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ የዘርፉን ስብራት ለማረቅ በተተገበረ የአሰራር ሥርዓት መሰረት ቴክኖሎጂን በመጠቀም የነዳጅ ስርጭትና ግብይትን ለማሳለጥ የአውቶሜሽን የቁጥጥር ስራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
ይሁን እንጂ ጥቂት ተዋንያን ለህዝባችንና ለሃገራችን የኢኮኖሚ እድገት የታለመ ሃብትን በስግብግብነት ለግል ጥቅማቸው ለማዋል በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ሰው ሰራሽ እጥረትን በመፍጠር መሆናቸውንና በዛሬ የምክክር መድረክ እነዚህን ህገወጥ አካላትን በትብብር በመለየት ተከታታይነት ያላቸው የማስተካከያ እርምጃዎችን ለመውሰድ የጋራ አቋም መያዙን አስታውቀዋል።




