የጅግጅጋ ሁለተኛው ደረጃ የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከል የመሠረተ ድንጋይ ተቀመጠ፤ ግንባታው በ3 ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል።
(ጅግጅጋ፤ ግንቦት 10 ቀን 2018 ዓ.ም) የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በሀገራችን ካሉት ክልሎች በከፍተኛ የእንስሳት ሀብት የሚታወቅ ሲሆን፣ ይህንን እምቅ ሀብት በአግባቡ በመጠቀም አርብቶ አደሩን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግና ለሀገር ምጣኔ ሀብት የሚኖረውን አስተዋጽኦ ከፍ ለማድረግ የሚያስችል አዲስ የልማት ፕሮጀክት በዛሬው ዕለት ተጀምሯል ።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ክቡር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ከሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ሙስጠፋ መሐመድ ጋር በመሆን በጅጅጋ ከተማ ለሚገነባው የ2ኛ ደረጃ የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከል የመሠረተ ድንጋይ አስቀምጠዋል ።
ክቡር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ ከ76 ሚሊዮን ብር በላይ በሚሆን ወጪ የሚገነባው ይህ ዘመናዊ ማዕከል በክልሉ ሁለተኛው የግብይት ማዕከል ነው ። ሰሞኑን በክልሉ የደጋሃቡር የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከል ተመርቆ ሥራ መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን፣ የጅግጅጋው ማዕከል ደግሞ በክልሉ ሁለተኛው ያደርገዋልም ብለዋል ።
ይህ የገበያ ማዕከል በዓለም ባንክ የፋይናንስ ድጋፍ በDRIVE ፕሮጀክት አማካኝነት የሚገነባ ሲሆን፣ በዘርፉ ያለውን የገበያ መሠረተ ልማት ስብራትን ከመጠገን ባለፈ አርብቶ አደሩ ከምርቱ ተገቢውንና ተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል ክቡር ሚኒስትሩ ።
በተጨማሪም የሀገሪቱን የወጪ ንግድ (ኤክስፖርት) ለማሳደግ ከፍተኛ አቅም የሚፈጥር ሲሆን፣ ይህም መንግሥት የንግድ ሥነ-ምህዳሩን እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ለማዘመንና ለመለወጥ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑ ተገልጿል ።
ክቡር ሚኒስትር ዶ/ር ካሳሁን ጎፌ፣ ይህ የልማት ፕሮጀክት በጣም በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ለሕዝቡ አገልግሎት መስጠት እንዲችል በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል ። ግንባታው በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ በውሉ መሠረት፣ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ያላቸውን ጽኑ እምነት አብራርተዋል ።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ክቡር ሙስጠፋ መሐመድ በበኩላቸው፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የክልሉን እምቅ አቅም ከግምት በማስገባት እያከናወናቸው ያሉ ፕሮጀክቶች ለክልሉ ሕዝብና መንግሥት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥሩ መሆናቸውን አብራርተዋል ።







