የኢዩ ካፌ ፕሮጀክት የስድስት ወራት አፈጻጸሙን ገመገመ፤ የቀጣይ ሶስት ወራት የትኩረት አቅጣጫዎችንም አስቀመጠ
አዲስ አበባ | መጋቢት 15/2018
በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ስር የሚንቀሳቀሰው የኢዩ ካፌ (EU-CAFÉ) ፕሮጀክት ላለፉት ሁለት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ አጠናቀቀ። በመድረኩ ላይ የፕሮጀክቱ ስድስት ወራት ጉዞ የተገመገመ ሲሆን፣ በቀጣይ ሶስት ወራት መጠናቀቅ ባለባቸው ተግባራት ላይም የጋራ መግባባት ተፈጥሯል።
በዚህ የግምገማ መድረክ ላይ የባለስልጣኑ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የክልል የቡናና ሻይ ተወካዮች፣ የምርምር ተቋማት ተወካዮች፣ የፕሮጀክቱ Focal Persons እና የፌዴራል ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የዋና ዳይሬክተር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰፊሳ አባቡ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ በሚደረግባቸው ወረዳዎች የቡናውን ዘርፍ ለማሳደግና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተስፋ ሰጪ ስራዎች ተከናውነዋል።
በባለፉት ስድስት ወራት የታቀዱ ተግባራት በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብና በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ እና በዘርፉ የሚታዩ ማነቆዎችን በመቅረፍ ረገድ ፕሮጀክቱ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑም ተመላክቷል።
ምንም እንኳን አፈጻጸሙ መልካም ቢሆንም፣ በቀሪዎቹ ሶስት ወራት ስራዎች በዝግታ እንዳይሄዱ አቶ ሰፊሳ የሚከተሉትን ማሳሰቢያዎች ሰጥተዋል፡-
1. ቅንጅታዊ አሰራር፦ ቀሪ ስራዎች ይበልጥ በተናበበ እና በተቀናጀ ሁኔታ መከናወን እንዳለባቸው።
2. የመረጃ አያያዝ፦ እስከ ዛሬ የተከናወኑ ተግባራት በበቂ መረጃ ተጠናቅረው ለቀጣይ ስራዎች እንደ ግብዓት እንዲያገለግሉ ማድረግ።
3. ውጤት ተኮር ስራ፦ በቀሩት ጥቂት ወራት ውስጥ በታቀዱት ግቦች ላይ በትኩረት በመስራት ፕሮጀክቱን በስኬት ማጠናቀቅ።
ማጠቃለያ፦ የኢዩ ካፌ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ የቡና ጥራትና ምርታማነት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት እየሰራ ያለ ፕሮጀክት ሲሆን፣ የአሁኑ ግምገማም የፕሮጀክቱን ውጤታማነት ለማረጋገጥ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተገልጿል።











