የኢትዮጵያና የኦማን የሁለትዮሽ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስርን የሚያጠናክር ውይይት ተካሄደ።
የኢትዮጵያ እና የኦማን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል ስትራቴጂያዊ ውይይት ተካሄደ። ውይይቱ የተካሄደው በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሀኪም ሙሉ (ዶ/ር) እና በኦማን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ሼክ ካሊፋ አሊ ኢሳ አል-ሀርቲ መካከል ነው፡፡
ሁለቱ ሀገራት እ.ኤ.አ. ከየካቲት 1995 ጀምሮ የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፣ ኦማን በአዲስ አበባ ኤምባሲዋን በ2017 መክፈቷ ይታወሳል፡፡ በውይይቱ ወቅት ዶ/ር አብዱልሀኪም እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያና ኦማን በቀይ ባህርና በህንድ ውቅያኖስ በኩል ባላቸው ታሪካዊ ትስስር ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ወዳጅነት አላቸው፡፡
የሁለቱ ሀገራት የንግድ ልውውጥ አወንታዊ እድገት እያሳየ ቢሆንም፣ የንግድ ሚዛኑ አሁንም ወደ ኦማን ያጋደለ መሆኑ በውይይቱ ተመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለችው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ለኦማን ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ዶ/ር አብዱልሀኪም አብራርተዋል ከ130 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላትን ኢትዮጵያ እንደ ትልቅ የገበያ መዳረሻነት የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በተለይም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ እና በኢንዱስትሪ ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች የተዘጋጁ የታክስ ነፃ መብቶችና ማበረታቻዎችን ዘርዝረዋል።
ኦማን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ሼክ ካሊፋ አሊ ኢሳ አል-ሀርቲ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በመልከአምድሯ፣ በአላት ሰፊ የገበያ እድል እና በተፈጥሮ ሀብቷ በጣም ተመራጭ ሀገር ናት ብለዋል፡፡





