የኢፈድሪ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ክቡር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የካዛክስታን ሪፐብሊክ አምባሳደር ዛልጎስ አዲባዬቭ ጋር በሁለቱ ሃገራት የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነት ጉዳዮች ዙሪያ ገንቢ ውይይት አድርገዋል።
በኢትዮጵያ እና በካዛክስታን መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በማደግ ላይ የሚገኝ መሆኑን የጠቀሱት ክቡር ሚኒስትሩ የንግድ ትስስርን በማጠናከር ለሁለቱ ሃገራት የላቀ ፋይዳ ወደሚያስገኝ ደረጃ መድረስ እንደሚገባ መግባባታቸውን አስታውቀዋል።
በሁለቱ ሃገራት ኢኮኖሚ መካከል ያለውን ከፍተኛ የንግድ እና የኢንቨስትመንት አቅምን አሟጠን ለመጠቀም በትብብር በምንሰራባቸው ጉዳዮች ላይም መወያየታቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በተገበረችው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርምና በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ማዕቀፍ ተመራጭ የንግድና ኢንቨስትመንት መዳረሻ በመሆኗ የካዛኪስታን ኩባንያዎች ሊሳተፉባቸው የሚችሉ መስኮችን ማብራራታቸውን ክቡር ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ካዛክስታን እ.አ.ኤ በ2015 የዓለም ንግድ ድርጅትን 162ኛ አባል ሆና ተቀላቅላለች። የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነትን ለማሳካት ለ7ኛው የስራ ቡድን ስብሰባ ዝግጅት በማድረግ ላይ በምንገኝበት በዚህ ወቅት ካዛኪስታን በባለብዙ ወገን ንግድ ያካበተችውን ልምድ እንደምታጋራን አምባሳደር ዛልጎስ አዲባዬቭ አረጋግጠዋል።







