የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት አገልግሎቶቹን በዲጂታል ቴክኖሎጂና በባለ 5 ኮከብ ፋሲሊቲዎች አዘመነ።
(አዲስ አበባ ፡ ግንቦት 13 ቀን 2018 ዓ.ም) የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት የአገልግሎት አሰጣጡን ያዘመኑ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሥራዎችንና የባለ አምስት ኮከብ ደረጃ ያላቸውን አዳዲስ መሠረተ-ልማቶች በይፋ መርቆ ሥራ አስጀምሯል።
የጥራት ማሻሻያ ፋሲሊቲዎቹን በይፋ የመረቁት የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ አንድ የጥራት ተቋም የውስጥ አደረጃጀቱና የአገልግሎት አካባቢው ራሱ የጥራት ምንነትንና ልህቀትን በተግባር ማሳየት አለበት በሚል መርህ የተከናወኑት እነዚህ ሥራዎች፣ ለሰልጣኞችና ለባለድርሻ አካላት ምቹ አካባቢን የፈጠሩና ከተቋማዊ ሪፎርሙ ጋር አብረው የሚሄዱ ናቸው።
በዕለቱ የተመረቁትና በአንድ ማዕከል የተደራጁት ፋሲሊቲዎች፦ እጅግ ዘመናዊ የድምፅና ቪዲዮ ሲስተሞች የተገጠሙለት “የጥራት አዳራሽ”፣ በባለ 5 ኮከብ ሆቴል ደረጃ የተደራጀው “የደረጃዎች ሬስቶራንት”፣ የከተማዋን ውብ የኮሪደር ልማትና የ“ጫካ” ፕሮጀክት ማራኪ እይታዎችን እያሳየ እንግዶች በጥራት ዙሪያ እንዲወያዩበት የተገነባው “የአብሮነት ካፌቴሪያ” እንዲሁም “ዘ ኤክሰለንስ ካፌ” ናቸው።
ሚኒስትሩ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተመዘገቡ ታሪካዊ ስኬቶችን ያነሱ ሲሆን፣ በተለይም በወጪ ንግድ አፈጻጸም ባለፉት 8 አመታት ከአራት ዕጥፍ በላይ አድጎ ከነበረበት 2.6 ቢሊየን ዶላር ባለፉት 10 ወራት 8.7 ቢሊዬን ዶላር መገኜቱን ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጠና ትግበራ ከተጀመረ ወዲህ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ መገኘቱንና በቅርቡም የዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) አባልነት ድርድር ስኬታማ በሆነ መልኩ መጠናቀቁን አስታውሰዋል። ለዚህ ውጤት መገኘትም የተቋሙ አመራርና ሠራተኞች የሚኒስቴሩን እሴቶች (መሰጠት፣ መቀናጀትና ማላቅ) በተግባር ማዋላቸውን ገልጸዋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር መሠረት በቀለ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ተቋሙ የውስጥ አቅሙን በማሳደግና በቴክኖሎጂ በመታገዝ ለሀገር ውስጥ ምርታማነትና ለዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸው፣ የተከናወኑት የሪኖቬሽን ሥራዎችም ከተቋሙ ተልዕኮ ባሻገር ተጨማሪ ገቢን እንደሚያስገኙ አብራርተዋል።
በመርኃ ግብሩ ላይ የኢፌድሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች፣ የደረጃ ቦርድ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።









