የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት የግብርና ቋሚ ኮሚቴ አባላትንና የክልል አመራሮችን በመጋበዝ የቀርጫንሼ ኃ/የተ/የግ/ድርጅትን የቡና ልማት ስራን ጎበኘ
ኅዳር 27/2018 ዓ.ም
አባያ ወረዳ/ ደበቃ ደቦቤሳ ቀበሌ
የቀርጫንሼን የቡና ልማትእንቅስቃሴን ለመቃኘት ባለስልጣን መስሪያቤቱ በተከበሩ አቶ ሰለሞን ላሌ ከተመራ ከሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት የግብርና ቋሚ ኮሚቴ እና የክልል አመራሮች ጋር በመሆን በድርጅቱ የእርሻ ማሳ ላይ ተገኝቶ ጎብኝቷል። በጉብኝት ወቅትም በድርጅቱ ኃላፊና ባለሞያዎች ሰፊ ገለጻ ተደርጓል። በገለጻውም ውሃ አጠቃቀማቸው ድሪፕ ኢሪጌሽን እንደሆነ፣ ከቴክኖሎጂ አንጻር ስማርት ቴክኖሎጂዎችን እንደሚጠቀሙ፣ መካናይዝ አመራረት ሂደት እየተከተለ እንዳለ ተገልጿል። በዚህም በሄክታር 62 ኩንታል ቡና እየተመረተ እንደሚገኝ ተነግሯል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት የግብርና ቋሚ ኮሚቴ እና የክልል አመራሮችና ባለሞያዎች በመጋበዝ ጉብኝቱን ማድረግ ያስፈለገው ተሞክሮውን ለማስፋት ለማስቻል እንደሆነ ተነግሯል። እነዚህ አካላትም ያዩትን ተሞክሮ የማስፋፋት ተግባርና ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠይቋል።
ከጉብኝቱ በኋላም ወደሐዋሳ በመመለስ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል። በውይይቱም ወቅትም ባለስልጣን መስሪያቤቱም ቀርጫንሼም ሰነድ አቅርበዋል። በቅድሚያ ሰነድ ያቀረቡት የየተከበሩ ዶ/ር አዱኛ ነበሩ። ሲያቀርቡም 90% በላይ ቡናን የሚያመርቱት አርሷደሮች እንደሆኑ፤ ወደ 30 ሚሊዮን በላይ ሕይወታቸው ቡና ላይ የተሞረኮዘ እንደሆነ ተናግረዋል። ቡና ለጂዲፒ 4% አስተዋጽኦ እንዳለው የገለጹት ባለስልጣኑ ቡና በግብርናው 40% በላይ ድርሻ እንዳለው አውስተው ለኤክስፖርት ከ30-35% ድርሻ እንዳለው አስታውሰዋል።
በማስከተልም ባለስልጣኑ በማልማቱም በኤክስፖርተሩም የሚሰራ እንደሆነና ከአርሷደር ጀምሮ እስከቡና ገዢዎች ጋር በጋራ እየሰራን ያለ መስሪያቤት እንደሆ ተናግረዋል። በዚህም ቡና ላይ ወደ 1.4 ሚሊየን መሬት ላይ ለማልማት ነው ሲሰራ ነው የቆየው ብለዋል። አፈጻጸሙ ወደ 1.2 ድረስ እንደተከናወነ፣ ከምርት አንጻር ወደ 1.3 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ቡና ለማምረት ታቅዶ ወደ 1.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን እንደተመረተ ተናግረዋል። ከምርታማነት አንጻር ያለውንም ሲገልጹ 9.4 ታቅዶ 10 ኩንታል በሄክታር ተመርቷል ብለዋል፤ ይህም 8.9 የነበረው ነው ሲሉ አክለዋል።
እነዚህን ውጤቶች ለማምጣት ፓኬጆች በሙሉ ሪቫይዝድ ተደርገው እንደሆነና ለአብነትም በሄክታር 2ሺ 500 ሲል የነበረው ፓኬጅ በተግባር ሲታይ ግን በአማካይ 1 ሺ 600 ሆኖ ስለተገኘ ይህን ወደ 4400 ከፍ ለማረግ አገራዊ ንቅናቄ ተዘጋጅቶ ፓኬጅ በመቅረጽ ስልጠናዎች ተሰጥተው ተሰርቷል ብለዋል። የተመረጡ ዘሮች ለአርሷደር ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነና የልምድ ልውውጦችን በማካሄድ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል። የተሻሻሉ ዝርያዎችን የማስፋት ስራዎች እንተሰሩና አግርኖሚክስ ፕራክትስ ላይ 100% ተከናውኖ ውጤቶቹ መጥተዋል ሲሉ አክለዋል። በመቀጠልም ግብአቶችን ከፕሮጀክቶች ጋር በመሆን የማሟላት ስራ እንደተሰራ ገልጸው ለአብነት ያክል 60 በ60 ለመቆፈር ብዙ ጊዜያት ሲፈጅ የነበረው አሁን ግን በነዳጅ የሚሰሩ መቆፈሪያዎች በመጠቀም በአንድ ደቂቃ አንድ ጉድጓድ ለመቆፈር አስችሏቸዋል ሲሉ አውስተዋል። የአውሮፖ ኅብረት ደምብ ላይ እስከ አርሷደር ድረስ ስልጠናዎች እንደተሰጡም አስታውሰዋል።
እንደ ዶ/ር አዱኛ ደበላ ሁሉ የቀርጫንሼ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር እስራኤል ደገፋ የበኩላቸውን ዕቅድ አፈጻጸም አቅርበዋል። ሲያቀርቡም 750 ሄክታር የቡና እርሻቸው በተደጋጋሚ እንደተጎበኘ በመግለጽ የጀመሩት ዶ/ር እስራኤል ደገፋ አሁን ላይ 5ሺ ሄክታር እየተስፋፋ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል። በአውት ግሮዎር እስክም 50 ሺ አርሷደሮችን አቅፈናል ሲሉም ተናግረዋል።
በማስከተልም አምስት እርሻዎች እንዳሏቸውና በ5 ዓመት ስትራቴጂ እሰከ15 ሺ ሄክታር መሬትን በከፍተኛ ቴክኖሎጂ ለማልማት እንደታቀደና አሁን ላይ 7ሺ 850 ሄክታር ለምቷል ብለዋል። ከ15 ሄክታሩ 90 ሺ ሜትሪክ ቶን ለማቅረብ እንደታቀደ ገልጸው እስካሁን ባለው ከ 5 ሺ በላይ ቡና ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳልተመረተ አስታውሰዋል።
የአመራረት ሂደታቸውን በገለጹበት ክፍልም ሲናገሩ ውሃ አጠቃቀማቸው ድሪፕ ኢሪጌሽን እንደሆነ፣ ከቴክኖሎጂ አንጻር ስማርት ቴክኖሎጂዎችን እንደሚጠቀሙ፣ መካናይዝድ አመራረትና የስማርት ቴክኖሎጂ የቡና ማቀናበሪያ እንዳላቸው፣ በዚህም ቡና በተመረተበት ቦታ የማቀናበር ስራ እየተሰራ እንደሆ ተናግረዋል። በስተመጨረሻም የተለያዩ ሰርቲፊኬሽኖች እንዳሏቸውና ባለፉት አስር ዓመታት ከ1.2 ቢሊየን በላይ ኤክስፖርት እንዳደረጉ ገልጸዋል።
ሁለቱ አካላት ሰነዶቻቸውን ካቀረቡ በኋላ የግብርና ቋሚ ኮሚቴ አባላትና የክልል አመራሮች ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል። በተሰነዘሩት ሀሳቦችም የቀርጫንሼ የቡና ልማት ሂደቱ ትራንስፎርሜሽን እሚባለውን በተግባር ያሳየ እንደሆነና ክልሎችና የግብርና ቋሚ ኮሚቴው የማስፋፋት ስራ እንዲሰሩ ተወስቷል።
በወቅቱ የሲዳማ ክልል አለታ ወንዶ ወረዳ ላይ ያለውን የኮምፖስት እና የክላስተር ልማት ምርጥ ተሞክሮ የተጎበኘ ሲሆን በሌላ የዜና እወጃችን ሙሉ ዘገባውን ይዘን የምንቀርብ መሆኑን እንገልጻለን።
አሸናፊ ጌታሁን ዘግቦታል።










