የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ ያለውን ተጽዕኖ ለማሳደግ.....
++++++++++++++
የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ ያለውን ተጽዕኖ ለማሳደግና የገበያ ተደራሽነቱን ለማስፋት የተለያዩ ስትራቴጂዎች ተነድፈው እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ለጋዜጣ ፕላስ እንደገለጹት፤ በዘርፉ በዓለም ገበያ የኢትዮጵያን ድርሻ ይበልጥ ለማሳደግ በተለይ በምርት ጥራት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ትልቋ የቡና አምራችና ላኪ ሀገር ስትሆን፣ በአሁኑ ወቅት የቡና ምርት ጥራትና የገበያ ተጽዕኖዋ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ በዘርፉ የተሰማሩ አርሶ አደሮችን ምርታማነት ለማሳደግ፣ አቅማቸውን መገንባትና የቡና ጥራትን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው፡፡ በዓለም አቀፍና በአፍሪካ ደረጃ ያላትን የገበያ መዳረሻ ለማስፋፋት ስትራቴጅዎች ተነድፈው መተግበራቸውን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ከፍተኛ መለኪያ የተቀመጠለት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በየካቲት ወር 2027 ዓ.ም 4ተኛውን የአፍሪካ የቡና ሳምንት በአዲስ አበባ የምታዘጋጅ ሲሆን፤ ይህም በቡና የሚኖረውን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ ነው፡፣ በተለይም አነስተኛ አምራቾችን ለማበረታታት፣ የቡና ምርት ጥራትን ለመጠበቅና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ሲሉም ገልጸዋል።
ጋዜጣፕላስ
