የኢትዮጵያ ብሔራዊ የንግድ ፖሊሲ ጸደቀ
Back

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የንግድ ፖሊሲ ጸደቀ

Motri
5 min read

በኢትዮጵያ የንግድ ታሪክ የመጀመሪያው የሆነውና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታችን ከተቋቋመ ከ118ዓመታት በኋላ አገራዊ የንግድ ፖሊሲ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቋል።

(አዲስ አበባ ፡ ግንቦት 18 ቀን 2018 ዓ.ም) የኢትዮጵያ የንግድ ዘርፍ የሚመራበት ወጥ ብሔራዊ የንግድ ፖሊሲ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ተዘጋጅቶ ዛሬ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በይፋ ጸድቋል ።

የንግድ ዘርፉ ለአጠቃላይ የሀገሪቱ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ዕድገት ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የላቀ አስተዋፅዖ እና የዕድገት አንቀሳቃሽ ሞተር ቢሆንም፣ እስካሁን ራሱን የቻለ ወጥ ፖሊሲ ባለመኖሩ የገቢና ወጪ ንግዱ ቅንጅትና መናበብ ሲጎድለው ቆይቷል ።

ቀደም ሲል ንግድን የሚመለከቱ የፖሊሲ ጉዳዮች በተለያዩ የሴክተር ፖሊሲዎች፣ አዋጆችና ደንቦች ውስጥ በተበታተነ ሁኔታ መገኘታቸው ዘርፉን በተሟላ ሁኔታ ለመምራት ትልቅ መሰናክል ሆኖ የቆየ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት የሀገሪቱ የንግድ ሥርዓት ፍትሃዊ ውድድር የሚጎድለው፣ የተለያዩ ሕገ-ወጥነትና ብልሹ አሠራሮች የበዙበት፣ እንዲሁም ሸማቾችን ያማረሩ የግብይት ሁኔታዎች የሚስተዋሉበት ሆኖ አልፏል ።

ከዚህም በተጨማሪ የወጪ ንግዱ በተበታተነ ሁኔታ በበርካታ ተቋማት የሚመራ በመሆኑ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪነቱን ማረጋገጥ ሳይችል መቆየቱ ይታወቃል ።

ይህንን ሰፊ ክፍተት ለመሙላት በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተዘጋጀውና ዛሬ የጸደቀው ታሪካዊው የንግድ ፖሊሲ፣ የነፃ ገበያ ሥርዓቱን በተሻለ ሁኔታ ለመምራትና የዘርፉን ተግዳሮቶች በዘላቂነት ለመፍታት ትልቅ ፋይዳ አለው ።

ፖሊሲው የተቀረፀው በአገሪቱ እየተገነባ ባለው የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ማዕቀፍ ውስጥ ሲሆን፣ ይኸውም የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓትን ወጥ በሆነ እሳቤ ለመምራት፣ የወጪ ንግድን በግብርና ምርቶች ላይ ካለው ጥገኝነት ማላቀቅ፣ የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችን ከዓለም አቀፍ ውድድር ለመጠበቅ ጊዜያዊ የታሪፍና የማበረታቻ ድጋፎችን ለመስጠት እንዲሁም የሸማቾችን መብትና ደህንነት በተደራጀ መልኩ ለማስጠበቅ ትልቅ መሠረት የሚጥል ነው ።

ፖሊሲው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የአስር ዓመቱን የልማት ዕቅድ መነሻ አድርጎ የተዘጋጀ በመሆኑ ሀገራዊ ፋይዳው እጅግ የጎላ ነው ።

ይህ ሰነድ በአሁኑ ወቅት መዘጋጀቱና መጽደቁ በንግዱ ማኅበረሰብ እና በግሉ ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ተገማችነትንና መተማመንን የሚፈጥር ሲሆን፣ የግሉ ዘርፍ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ዋና ሞተር ሆኖ እንዲያገለግል መንግሥት ምቹ ከባቢያዊ ሁኔታን እንደሚፈጥር ይታመናል ።

በተለይም የንግድ ሕጎች፣ ደንቦችና አሠራሮች በየጊዜው ከመለዋወጥ ወጥተው፣ ለሁሉም የንግድ ተዋናዮች ግልጽ፣ ተጠያቂነት የሰፈነባቸውና ቀድሞ "ተገማች" እንዲሆኑ የሚያደርግ በመሆኑ፣ የግሉ ዘርፍ ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም አቀፍ የንግድ ምህዳር ውስጥ የረጅም ጊዜ ዕቅዶቹን በተረጋጋ ሁኔታ እንዲመራና ኢንቨስትመንቱን እንዲያሰፋ ሙሉ መተማመንን ይፈጥርለታል ።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የምታካሂደውን የዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) አባልነት ድርድር፣ የአህጉራዊ (AfCFTA) እና የቀጣናዊ የንግድ ስምምነቶች ውህደትን ወጥ በሆነ እሳቤ ለመምራት የሚያስችል ይፋዊ ሰነድ በመሆኑ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን (FDI) በመሳብ ረገድ ለዓለም አቀፍ ነጋዴዎችና ባለሀብቶች ከፍተኛ ተገማችነትን የሚሰጥ ነው ።

Gallery

Gallery image 1

Tags

#Motri#coffee