የኢትዮጵያ እና የአልጀሪያን የንግድ ግንኙነት ለማሳደግ ያለመ ውይይት ተካሄደ
ኢትዮጵያና አልጀሪያ ያላቸውን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ወደ ላቀ የንግድና ኢኮኖሚ ትብብር ለማሸጋገር የሚያስችል ውይይት በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ተካሄደ።
ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የወጪ ንግድ ምርት ወደ አልጀሪያ ገበያ በስፋት ለማቅረብ የሚረዱ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር የውይይቱ ዋነኛ ትኩረት ነበር። ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ የስሚን ውሀብረቢ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ጥራት ያላቸውን ምርቶች ለአልጀሪያ ገበያ የማቅረብ ከፍተኛ ፍላጎትና አቅም አላት።
ውይይቱ የተካሄደው በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የንግድ ትስስርና ወጪ ንግድ ፕሮሞሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ የስሚን ውሀብረቢ እና በኢትዮጵያ የአልጀሪያ አምባሳደር ዶ/ር መሀመድ ካሊድ መካከል ነው። በውይይቱ ወቅት የሁለቱን ሀገራት የንግድ ልውውጥ መጠን ለማሳደግ በሚያስችሉ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ በዝርዝር መክረዋል።
አምባሳደር ዶ/ር መሀመድ ካሊድ በበኩላቸው የኢትዮጵያና የአልጀሪያ ግንኙነት ስትራቴጂካዊ መሆኑን ጠቅሰው ከንግድና ኢኮኖሚ ባለፈ በባህል፣ በማህበራዊ እና በዲፕሎማሲያዊ ዘርፎችም ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ይህንን ትብብር ወደ ተግባር ለመለወጥም በቅርብ ወራት ውስጥ “የኢትዮ-አልጀሪያ የንግድ ፎረም” እና የንግድ ባዛር በአዲስ አበባ ለማካሄድ ስምምነት ላይ ተደርሷል።
ይህ የንግድ ፎረም እና ባዛር የሁለቱን ሀገራት የንግድ ማህበረሰብ በቀጥታ በማገናኘት፣ አዳዲስ የገበያ ትስስሮችን ለመፍጠርና የሁለትዮሽ የንግድ ልውውጡን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ትልቅ አጋጣሚ እንደሚፈጥር ተገልጿል።









