ሀገር-በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ለንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ ተገለጠ።
(አዲስ አበባ፣ መጋቢት 07 ቀን 2018 ዓ.ም) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ክቡር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ተገኝተው “ኢትዮጵያ - አዲሷ የኢንቨስትመንት መዳረሻ” በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል።
ክቡር ሚኒስትሩ በንግግራቸው፤ በብዝሃ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የተመሰረተው ሀገር-በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ለውጭ ንግድና ኢንቨስትመንት ተገማችና ምቹ ሥነ-ምህዳር መፍጠሩን ገልጸዋል።
በተለይም የፋይናንስ ሴክተር ሪፎርም፣ የካፒታል ገበያ ሥርዓት መዘርጋት፣ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጠና (AfCFTA) ትግበራ እና የዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) አባልነት ስኬታማ ጉዞ ለባለሀብቶች አስተማማኝ ዋስትናና ሰፊ ገበያ እየፈጠሩ ያሉ ስኬቶች መሆናቸውን አብራርተዋል።
ሪፎርሙ ያመጣቸውን ትሩፋቶች ለዓለም ማህበረሰብ በማስገንዘብ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ የሚዲያ ሚና ከፍተኛ መሆኑን የጠቀሱት ክቡር ሚኒስትሩ፤ ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በቅርቡ ስራ ያስጀመረው "የፐልስ ኦፍ አፍሪካ" (POA) ቴሌቪዥን ቻናል የአፍሪካ ትርክት በአፍሪካዊያን እንዲነገርና የአህጉሪቱን የጋራ ብልጽግና ለማረጋገጥ ያለውን ፋይዳ አድንቀዋል።
ተቋሙ ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችንና አሠራሮችን በመተግበር ያሳየው ለውጥና የታሪክ አንኳር ተግባራትን በጋለሪ ሰንዶ ማስቀመጡ ለሌሎች ተቋማት አርአያ የሚሆን ተግባር መሆኑም ተገልጿል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መሰል የሚዲያ መድረኮችን በመጠቀም የሀገራችንን የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድሎች የማስተዋወቅ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተመልክቷል።
ሚኒስትሩ የኢዜአን የዘመናት ጉዞ የሚያስቃኘውን ጋለሪም ጎብኝተዋል









