የእንስሳት ወጪ ንግድ ገቢን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 6፣ 2018 ከእንስሳት ወጪ ንግድ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው ሲሊ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
ሚኒስትሩ እንዳሉት ÷ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ከወጪ ንግድ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው፡፡
በሀገሪቱ ያለውን እምቅ ሃብት በመጠቀምና ጥራት ያለው ምርት ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማጠናከር በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡
በተለይም ከእንስሳት ወጪ ንግድ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የዘርፉን የንግድ ሰንሰለት ከማዘመን ጀምሮ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ ካላት የእንስሳት ሃብት አንጻር የምታገኘው ገቢ አነስተኛ መሆኑን ጠቁመው ÷ ለዚህም የእንስሳት ሕገ ወጥ ንግድ ዋነኛው ተግዳሮት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ችግሩን ለመፍታትም ሚኒስቴሩ ዘመናዊ የእንስሳት ግብይት ማዕከላትን በተለያዩ አካባቢዎች እየገነባ እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡
ለአብነትም በኦሮሚያ፣ ሶማሌና አፋር ክልሎች የተጀመሩት የግብይት ማዕከላት ግንባታ 75 በመቶ መድረሱን ጠቁመው÷ በቀጣይ 2 ወራት ውስጥ ተጠናቅቀው ሥራ እንደሚጀምሩ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በኦሮሚያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ ሶማሌ እና አፋር ክልሎች ዘመናዊ የእንስሳት ግብይት ማዕከላት ግንባታ እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
በቀጣይ የዘርፉን ምርታማነት በማሳደግና የንግድ ሥርዓቱን በማዘመን የሚገኘው ገቢ ለማሳደግ ሁሉም የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡
ኤ ኤም ሲ




