የቡናና ሻይ ባለስልጣን ስልጠና
Back

የቡናና ሻይ ባለስልጣን ስልጠና

ECTA
5 min read

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ለኢንዱስትሪ ባለቤቶችና ባለሙያዎች ስልጠና ሰጠ

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ለኢንዱስትሪ ባለቤቶችና ባለሙያዎች ስልጠና ሰጠ ግንቦት 12/2018 ዓ.ም (አዲስ አበባ)፡ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና ግልጽነትን ለማስፈን ያለመ ሰፊ የስልጠና መድረክ አካሄደ። በባለስልጣኑ ትልቁ አዳራሽ በሁለት ዙር በተሰጠው በዚህ ስልጠና ላይ ከ800 በላይ የኢንዱስትሪ ባለቤቶችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የገበያ ልማትና ቁጥጥር ዘርፍ ኃላፊ ክቡር አቶ ሻፊ ዑመር፤ ተቋሙ የዘርፉን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረጉ ማሻሻያዎችን እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

"ይህ ስልጠና ተገልጋዮች ካሉበት ቦታ ሆነው ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል የምናደርገው የሪፎርም ስራ አካል ነው" ያሉት አቶ ሻፊ፣ "ዓላማችን በየደረጃው ያለውን አላስፈላጊ መንገላታት በማስቀረት፣ ግብይቱንና የኤክስፖርት ሂደቱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መደገፍ ነው" ብለዋል።

የስልጠናው ዋና ዋና ትኩረቶች፡

ዲጂታል አገልግሎት፡ ተገልጋዮች በአካል መገኘት ሳያስፈልጋቸው ባሉበት ቦታ ሆነው አገልግሎት የሚያገኙበት አሰራር።

የቴክኖሎጂ ክትትል፡ ከግብይት ስራ ጋር ተያይዞ ምርቶችን በቴክኖሎጂ የታገዘ ክትትል (Tracking) ማድረግ።

የመጋዘን ቁጥጥር፡ በመጋዘኖች ውስጥ ያለውን የቡናና ሻይ ክምችት በአግባቡ ለመቆጣጠር የሚያስችል ስርዓት።

የሽኝት ቁጥጥር፡ የምርቶች ሽኝት በዘመናዊ መንገድ እንዲከናወንና ህገወጥ ድርጊቶችን በቀላሉ ለመለየት የሚያስችል አሰራር።

አቶ ሻፊ አክለውም፣ አዲሱ አሰራር በዘርፉ የሚታዩ ህገወጥ እንቅስቃሴዎችን ከመግታት ባለፈ፣ ለላኪዎችና ለኢንዱስትሪ ባለቤቶች ስራን የሚያቀልና ግልጽነትን የሚፈጥር መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል። ተሳታፊዎችም የተገኙትን የቴክኖሎጂ አማራጮች በመጠቀም ለዘርፉ እድገት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ይህ ሰፊ ስልጠና ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የኢትዮጵያን የቡናና ሻይ ምርት በዓለም አቀፍ ገበያ ይበልጥ ተወዳዳሪ ለማድረግና የንግድ ስርዓቱን ለማዘመን የጀመረው ስራ አካል መሆኑ ተገልጿል።

Gallery

Gallery image 1
Gallery image 2
Gallery image 3
Gallery image 4
Gallery image 5
Gallery image 6

Tags

#ECTA#coffee