የብራዚል ሪል መዳከም በቡና ዋጋ ላይ ጫና አሳደረ!!
ግንቦት 20/2018
በብራዚል የገንዘብ ምንዛሬ (ሪል) ላይ የታየው መዳከም፣ የዓለም አቀፍ የቡና ዋጋ እንዲቀንስ ምክንያት ሆኗል። ረቡዕ ዕለት በዋለው የገበያ ግብይት፣ የሐምሌ ወር የአረቢካ ቡና ውል (KCN26) በ -4.15 (-1.51%) የቀነሰ ሲሆን፣ የሮቡስታ ቡና (RMN26) ደግሞ -47 (-1.34%) ዝቅ ብሎ ተዘግቷል።
የዋጋ መውረድ ምክንያቶች
• የምንዛሬ ተጽዕኖ፦ የብራዚል ሪል የመግዛት አቅም ባለፈው አንድ ሳምንት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ መዳከሙ፣ የብራዚል ቡና አምራቾች ምርታቸውን በስፋት ወደ ውጭ እንዲልኩ አበረታቷቸዋል። ይህ ከፍተኛ አቅርቦት ደግሞ በገበያው ላይ የዋጋ መውረድን አስከትሏል።
• የአቅርቦት ትንበያ፦ የተለያዩ ተቋማት (እንደ StoneX እና Marex ያሉ) የብራዚል የ2026/27 የቡና ምርት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምርና ታሪካዊ ሪከርድ ሊሰብር እንደሚችል መተንበያቸው ለዋጋው መውረድ ሌላው ምክንያት ነው።
ዋጋውን የደገፉ ተቃራኒ ሁኔታዎች
ምንም እንኳን የሪል መዳከም ዋጋውን ቢያወርደውም፣ አንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ ዋጋው በጣም እንዳይቀዘቅዝ ደግፈው ይዘውታል።
• የአየር ንብረት ስጋት፦ በቬትናም ያለው ደረቅ አየር በሮቡስታ ቡና ምርት ላይ ስጋት ፈጥሯል። በተጨማሪም የ"ኤል ኒኞ" (El Niño) የአየር ሁኔታ ክስተት በብራዚል የቡና ዛፎች አበባ በሚያወጡበት ወቅት ዝናብ ሊያዘገይ ይችላል የሚለው ስጋት ለዋጋው መረጋጋት ድጋፍ ሆኗል።
• የመጋዘን ክምችት መቀነስ፦ በአይሲኢ (ICE) መጋዘኖች ያለው የቡና ክምችት ላለፉት ሁለት ወራት እየቀነሰ መምጣቱ በገበያው ላይ ጥረት እንዳለ አመላካች ሆኗል።
• የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ መዘጋት፦ በዚህ መስመር ላይ ያለው የትራንስፖርት መስተጓጎል የመርከብ ዋጋን፣ የኢንሹራንስ እና የነዳጅ ወጪን በመጨመሩ፣ በተዘዋዋሪ የቡና ዋጋ ላይ የራሱ የሆነ ጫና ፈጥሯል።
የወደፊት እይታ
እንደ ዓለም አቀፉ የቡና ድርጅት (ICO) እና የዩኤስዲኤ (USDA) ዘገባዎች ከሆነ፣ የዓለም የቡና ምርት በ2025/26 የምርት ዘመን የ2 በመቶ ጭማሪ ሊያሳይ እንደሚችል ይጠበቃል። በተለይም የሮቡስታ ቡና ምርት የ10.9 በመቶ ከፍተኛ ጭማሪ ያሳያል ተብሎ ቢታሰብም፣ የአረቢካ ምርት ግን በ4.7 በመቶ ሊቀንስ እንደሚችል ተገምቷል።
ባጠቃላይ የቡና ገበያው በምንዛሬ መዋዠቅ፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና በጂኦ-ፖለቲካዊ ውጥረቶች መካከል ሆኖ ከፍተኛ ትንቅንቅ እያስተናገደ ይገኛል።
ምንጭ አድርጌ የወሰድኩት https://www.barchart.com/ ነው፡፡
ሳህለማርያም ገ/መድህን
