የቡና ጥራትና ምርታማነት ስልጠና
Back

የቡና ጥራትና ምርታማነት ስልጠና

ECTA
5 min read

📌 የቡናችንን ጥራትና ምርታማነት ወደ ላቀ ደረጃ! ☕️🇪🇹

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የቡናን እሴት ሰንሰለት ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው የሚቃኝ ሰፊ የስልጠና መድረክ በሀዋሳ እና በጅማ ከተሞች ጀምሯል።

በኢትዮጵያ የቡና ጥራትና ምርታማነትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ያለመ ሰፋ ያለ የባለሙያዎች ስልጠና በሀዋሳ እና በጅማ ከተሞች በጋራ መጀመሩ ተበሰረ። የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ታጋይ ኑሩ በሀዋሳው መድረክ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፣ ስልጠናው ልዩ የሚያደርገው የቡናን እሴት ሰንሰለት ከመጀመሪያው የምርት ሂደት ጀምሮ እስከ ግብይት ድረስ ያለውን ሙሉ ጉዞ የሚያካትት ሆኖ መዘጋጀቱ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ የተቀናጀ ስልጠና በስራ ላይ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ እና የቡናን ጥራት በዘላቂነት ለመጠበቅ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት አፅንዖት የሰጡት ክቡር አቶ ታጋይ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የምርት መጠኑን ለመጨመር እና የጥራት ደረጃን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ስትራቴጂካዊ ፓኬጆችን ቀርጾ ወደ ትግበራ መግባቱን አስረድተዋል። እነዚህን ዘመናዊ አሰራሮችና ቴክኖሎጂዎች ውጤታማ ለማድረግ ግንዛቤው እስከ ታችኛው አርሶ አደር ድረስ መድረስ እንዳለበት በመግለጽ፣ ለዚሁ ተልዕኮ ተብሎ የተነደፉ ፕሮጀክቶች ተነድፈው በስፋት እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል። ይህም የሀገሪቱን የቡና ዘርፍ ተወዳዳሪነት ለማረጋገጥ የመንግስትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑንም ምክ/ዋና ዳይሬክተሩ በአጽንዖት ተናግረዋል።

የሲዳማ ክልል ቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ቃሬ በበኩላቸው፣ ቡና ለክልሉ ከመጠጥነት ባለፈ ማህበራዊ ትስስርን የሚያጠነክር ታላቅ እሴት መሆኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት በቡና ኤክስፖርት ያስመዘገበችው ውጤት አኩሪ እንደሆነ አስረድተው፤ ሆኖም እንደ ብራዚልና ቪየትናም ካሉ ግዙፍ አምራች ሀገራት ጋር ሲነጻጸር ግን በምርታማነትና በውጭ ምንዛሪ ግኝት በኩል ገና ብዙ ስራ እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል።

"እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል ጠንክረን መስራት ያለብን አሁን ላይ ነው" በማለት ለተሰብሳቢዎቹ ጥሪ አቅርበው፤ በአሁኑ ወቅት በሲዳማ ክልል በሄክታር 10.13 ኩንታል የሆነውን የምርታማነት መጠን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አቶ መስፍን ጨምረው ገልጸዋል።

ሲዳማ ክልል ለማዕከላዊ ገበያ የሚያቀርበው ቡና ደረጃ አንድ እና ሁለት መሆኑ በስልጠናው ላይ የተጠቆመ ሲሆን የጥራት ደረጃውን ይበልጥ ለማሻሻልና የምርት ግኝቱን ለማሳደግ ስልጠናው የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑ ተገልጿል። ይህ ንቅናቄ የኢትዮጵያን ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ያለውን የበላይነት ለማስጠበቅ አዲስ ተስፋ የሰነቀ በመሆኑ ስልጠናውን ላዘጋጀው የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ልማት ፕሮግራም FOLUR ፕሮጀክት በተሳታፊዎች በኩል የላቀ ምስጋና ቀርቧል።

በስልጠናው ላይ ከሲዳማ፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞን እና ወረዳዎች የተውጣጡ 150 በላይ አርሶ አደሮች፣ የልማት ጣቢያ ባለሙያዎች እንዲሁም በቡና ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

Gallery

Gallery image 1
Gallery image 2
Gallery image 3
Gallery image 4
Gallery image 5
Gallery image 6
Gallery image 7
Gallery image 8
Gallery image 9
Gallery image 10
Gallery image 11
Gallery image 12

Tags

#ECTA#coffee