የቡና ገበያ ሲናወጥ
Back

የቡና ገበያ ሲናወጥ

ECTA
5 min read

☕ የቡና ገበያ ሲናወጥ፡ ዘላቂ አጋርነት የውድድር ብልጫ አለው!!

በሳህለማርያም ገ/መድህን

ባለፈው አንድ ዓመት የዓለም አቀፉ የቡና ኢንዱስትሪ ላለፉት አሥርተ ዓመታት አይቶት የማያውቀውን ከፍተኛ የዋጋ መዋዠቅ አስተናግዷል። የዋጋ ጣራ መንካት፣ የአሜሪካ የንግድ ታሪፎች እና የአውሮፓ ህብረት አዲሱ የደን ጥበቃ ደንብ (EUDR) ብዙ የቡና ድርጅቶች ስለ አቅርቦት ዋስትና፣ ስለ ዋጋ ስልቶች እና ስለ ረጅም ጊዜ ዕቅዳቸው ደጋግመው እንዲያስቡ፣ እንዲያጤኑ አስገድዷቸዋል።

⚠️ 2025፡ የኢንዱስትሪው የፈተና ዓመት

ያለፈው ዓመት የገበያ ሁኔታ፣ የዋጋ መከላከያ ዘዴዎች (hedging tools) ለሌላቸው አነስተኛ ቆዪ ኢንዱስትሪዎች እጅግ ፈታኝና ውጣ ውረድ የበዛበት ነበር። ለዚህ አለመረጋጋት ደግሞ ዋና ምክንያቶች የሚከተሉት ነበሩ፦

የጦዘ እና ሪከርድ የሰበረ የቡና ዋጋ ንረት፣

በሚያዝያ 2025 በብራዚል ቡና ላይ የተጣለው የ50% የአሜሪካ ታሪፍ፣

የዓለም አቀፍ ንግድን ያወከ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ እንዲሁም

ከዋና ዋና አምራች አገራት የሚመጣው አቅርቦት መቀነስ።

ምንም እንኳን ቡናው ከታሪፍ ነፃ ቢደረግም፣ የተፈጠረው ድንጋጤ ግን የንግድ ምንጭ አሰባሰብ ስልቶችን ሙሉ በሙሉ እንዲቀየሩ አድርጓል።

🤝 የጥብቅ ግንኙነት አስፈላጊነት/ Strategic and strong partnership

በእንዲህ ያለ አስቸጋሪ ወቅት በቆዪዎች፣ በአልሚዎች፣ ላኪዎች እና በአምራች ገበሬዎች መካከል ያለው የረጅም ጊዜ አጋርነት ከምንጊዜውም በላይ ወሳኝ ይሆናል። በመተማመን፣ በግልጽነት እና በመረጃ ልውውጥ ላይ የተገነባ ግንኙነት፤ ገበያው በሚዋዥቅበት ወቅት እንኳ ድርጅቶች በአስተማማኝ መሠረት ላይ እንዲቆሙ፣ አቅርቦት እንዲያገኙ፣ ጥራትን እንዲጠብቁ እና ስጋቶችን እንዲቀንሱ ይረዳቸዋል። የአቅርቦት ሰንሰለቱ ሲወጣጠርና ዋጋ ሲንር፣ እነዚህ የቆዩ ጥብቅ ግንኙነቶች የንግድ ሥራው ሳይስተጓጎል እንዲቀጥል ያደርጋሉ። በተለይ ጥራት፣ ጥራት፣ ጥራት።

📉 በ2026 የሚታዩ አዳዲስ ዕድሎች

ወደ 2026 ስንገባ ገበያው እንደ ዓለም አቀፉ የቡና ድርጅት (ICO) ጥር 2026 ሪፖርት፦

የቡና ገበያ ዋጋ (C market) ከነሐሴ 2025 ወዲህ ዝቅተኛው ደረጃ ላይ ደርሷል፣

በብራዚል የታየው የተሻለ የአየር ሁኔታ የዓለም አቅርቦት ገበያውን ሰፊ የአቅርቦት መጠን እንዲኖረው አድርጎታል። ነገር ግን ደግሞ ይህን ለውጥ ለበጎ ነው ብሎ መቀበል የብልሆች ምርጫ ነው። በንግድ አለም ብዙ ጊዜ ማትረፍ እንዳለ ሁሉ አንዳንዴ ደግሞ ትንሽ ትርፍ አልያም ደግሞ በዋና መሸጥ፣ እልፍ ካለም በጥቂት ኪሳራ መሸጥ ይጠበቃል። ይህ ተፈጥሯዊ፤ ያለ፣ የነበረ ወደ ፊትም የሚኖር የንግድ ዑደት ነው።

ይህ ለውጥ ድርጅቶች ወጪያቸውን እንዲያመጣጥኑ፣ በመረጃ ላይ የተመሠረተ የብልህ አካሄድ እንዲኖራቸው እና የረጅም ጊዜ የቡና ምንጭ ስልቶችን እንዲያቅዱ አዲስ በር ከፍቷል። ቀደም ብለው በአቅርቦት ሰንሰለቱ ውስጥ ጠንካራ አጋርነት የፈጠሩ ኩባንያዎች፣ ገበያው ወደ መረጋጋት ሲመለስ ራሳቸውን በተሻለ ሁኔታ ለማላመድና ጥራቱን የጠበቀ አቅርቦት ለማረጋገጥ ዝግጁ ያደርጋቸዋል ።

📈 ከኢንዱስትሪው ምን እንማር?

ተለዋዋጭ ገበያዎች የሚያስተምሩን ትልቁ ቁምነገር፦ ቡና ማለት ዋጋ ብቻ ሳይሆን ግንኙነት፣ ግልጽነትና የረጅም ጊዜ መተማመን መሆኑን ነው። በጠንካራ አጋርነት ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን ያፈሰሱ ድርጅቶች፣ የቡና ገበያውን የወደፊት ጉዞ በስኬት ለመወጣት የተሻለ ቁመና ላይ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።

መንግስት የዜጎቹ በተለይም ደግሞ የቡናው ተዋናይ ዘለቄታዊ ኑሮ ያስጨንቀዋል፣ ያሳስበዋል። ለዚህም ነው እስከዛሬ አርሶ አደሩ የተሻለ ኑሮ እንዲኖር፣ ዘርፉም ወደላቀ ደረጃ እንዲደርስ ሌት ተቀን የሚደክመው። ይህ ጥረት ዛሬም፣ ነገም ከነገወዲያም ተጠናክሮ ይቀጥላል። የምርት ዘመኑ መግቢያ ላይ የአለምን የገበያ አዝማሚያ በመመልከት ክቡር የግብርና ሚኒስትሩ አቶ አዲሱ እና የባለስልጣን መ/ቤቱ ዋና ዳ/ር ዶ/ር አዱኛ መላ ባለድርሻ አካላትን ሰብስበው የጥንቃቄ መልዕክት አስተላልፈው ነበር። በዚህም የገባቸው አብዝተው ተጠቀሙ። አሁንም ብልጥ ከሰራው ስህተት ፈጥኖ ይማራልና የዋጋው ሁኔታ ከዚህም በላይ የከፋ ሁኔታ ላይ ሳይደርስ ቡናን ወደማዕከላዊ ገበያ አቅርቦ ከኪሳራም ሆነ ከተጠያቂነት መዳን ይቻላል። አንድ በዚሁ ዘርፍ የተሰማሩ ወዳጄ ያካፈሉኝን መልዕክት ጠቁሜ ፅሁፌን ላብቃ።

"ባለፈው አመት በዘመኔ አይቼው የማላውቅ ትርፍ አተረፍኩ። ዘንድሮም ያ ይደገማል የሚል ተስፋ ቢኖረኝም የቡና ገበያ የጨዋታ ህግ ተለዋዋጭ መሆኑን ስለማውቅ የበለጠ ከኪሳራ ለመዳን ስል እጄ ላይ የሚገኘውን ምርት አውጥቼ መሸጥ ችያለሁ። በዚህ ፈታኝ ወቅት መንግስት እያቀበለን ላለው መረጃ እና የውይይት መድረኮች የላቀ ክብር እና አድናቆት አለኝ''

Gallery

Gallery image 1

Tags

#ECTA#coffee