በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት መሠረት ዕሴት የታከለበት ቡናን መላክ ተጀምሯል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 30/2018
በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት መሠረት ዕሴት የታከለበት የኢትዮጵያ ቡናን ለአፍሪካ ሀገራት ገበያ መላክ መጀመሩን የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።
የአፍሪካ ሕብረት መረጃ እንደሚያሳየው የአፍሪካ ሀገራት 85 በመቶ ምርታቸውን ለአውሮፓ፣ እስያ፣ ሰሜንና ላቲን አሜሪካ ገበያ የሚልኩ ሲሆን በአንፃሩ የእርስ በእርስ የንግድ ልውውጣቸው ከ15 በመቶ ያልበለጠ ነው።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራም የሀገራቱን የእርስ በእርስ የንግድ ትስስር በማሳለጥ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን እንደሚያሳደግ ታምኖበታል።
አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነቱም የአፍሪካ ሀገራትን የንግድ ታሪፍና መሰናክል በማስወገድ ወጥ በሆነ የአሰራር ሥርዓት የእርስ በእርስ የገበያ ትስስርን ማሳለጥ ዋና ዓላማው ያደረገ ነው።
ይህም የአህጉሪቱን አባል ሀገራት የንግድ ልውውጥ በማሳደግ፣ የኢንዱስትሪ ዕድገትን በማፋጠንና ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር የአፍሪካን ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳለጥ ከፍተኛ ፋይዳ አለው።
በዚህም ኢትዮጵያ በአህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነቱ መሰረት ከመስከረም 29 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ገበያ ምርቶችን መላክ ጀምራለች።
የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሻፊ ዑመር ለኢዜአ እንዳሉት፤ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ሥምምነት መሰረት የኢትዮጵያ ቡና ገበያ መዳረሻን ለማስፋት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የአፍሪካን ሰፊ የገበያ ዕድል ለመጠቀም የኢትዮጵያን ጥሬ ቡና ከመላክ ይልቅ ዕሴት ጨምሮ ለማቅረብ ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል።
በዚህም በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ዕሴት የተጨመረበትን ቡና የመላክ ጅማሮን የበለጠ ለማስፋት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ አዳዲስ የቡና ገበያ መዳረሻዎችን እያሰፋች ነው ያሉት አቶ ሻፊ፤ ለአብነትም በ2016 ዓ.ም የኢትዮጵያን የቡና ገበያ መዳረሻ ከ64 ሀገራት በ2017 ዓ.ም ወደ 84 ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
የኢትጵያን ነባር የቡና ገበያ መዳረሻን በማጠናከርና አዳዲስ ገበያን ለማስፋት በተለያዩ ሀገራት ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
ቻይናን ጨምሮ አስር የእስያ ሀገራት የኢትዮጵያን ቡና እየገዙ እንደሚገኝ ጠቁመው በቀጣይም ቡና ላይ ዕሴት በመጨመር የአፍሪካ እና እስያ ገበያን ለመጠቀም ከኢትዮጵያ ቡና ላኪዎችና የአውሮፓ ባለሃብቶች ጋር በመቀናጀት ዕሴት ጨምሮ መላክ ላይ እንዲሳተፉ ይሰራል ብለዋል።


