ጥቅምት 17/2018
ይህ የተገለጸው ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልከውን ቡና በተመለከተ በባለፉት ሶስት ወራት በተከናወነው ዕቅድ አፈጻጸም ላይ ክቡር የግብርና ሚኒስትሩ አቶ አዲሱ አረጋ በተገኙበት በዛሬው ዕለት በስካይ ላይት ሆቴል በተካሄደ የውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡ በውይይቱ ላይ ክቡር ዶ/ር አዱኛ ደበላ የባለስልጣን መ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ ሌሎች የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ቁጥራቸው ከ140 የሚልቅ ላኪዎች እና ሌሎች የቡና ቤተሰቦች ተገኝተዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትሩ መንግስት ዘርፉን ለመደገፍ፣ ለማበረታታት እና ወደፊት ለመግፋት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመው ላኪዎችን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት በታማኝነት እና በትጋት በመስራት አ/አደሩ ተጠቃሚ የሚሆንበትን እና አገራችንም በዘርፉ የላቀ ደረጃ እንድትደርስ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡ በልማቱ በኩል ዘመናዊ እና ቀልጣፋ የአመራረት ዘይቤ መከተል እንደሚገባ የጠቆሙት ክቡር ሚኒስትሩ በበጀት ኣመቱ በመንግስት የተቀመጠውን የበጀት ዓመቱን ዕቅድ ለማሳካት በተቀናጀ ሁኔታ የተጠናከረ ስራ መስራት እንደሚጠበቅ እና ባሉ ችግሮችም ዙሪያ በግልጽ ተወያይቶ አቅጣጫ እንደሚቀመጥ ተናግረዋል፡፡
ክቡር ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አዱኛ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ዘንድሮ 600 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 3 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት እየሰራች መሆኗን የገለጹ ሲሆን በሩብ አመቱ 152 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጪ በመላክ 622.5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 114 ሺህ ቶን ቡና በመላክ 762.5 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ማግኘት እንደተቻለ ተናግረዋል። ገቢው ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ47 በመቶ ዕድገት የተመዘገበበት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ክቡር አቶ ሻፊ ዑመር የባለስልጣን መ/ቤቱ ምክ/ዋና ዳ/ር እና የግብይት ዘርፍ ኃላፊ የሶስት ወራት የቡና እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን በቀረበው ሪፖርት ላይ ሰፊ ውይይት ከተካሄደ በኋላ የወጪ ንግድ መጠን የማሳደግ ጉዳይ ትኩረት ማግኘት እንዳለበት እንዲሁም በቡና የወጪ ንግድ የአመቱን ግብ በመጠን እና በውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማሳካት በቡና ዕሴት ሰንሰለት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በተቀናጀ አሰራር ለመፍታት መግባባት ላይ ተደርሶ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡











