የአካል ጉዳተኞች በስራ ስምሪት፣ በግብርና፣ በትምህርትና ዘርፍ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት መልካም ጅምሮች ቢኖሩም ገና ብዙ መስራት የሚጠይቅ መሆኑን የጉዳዩ ባለቤቶች ገለጹ።
አዳማ ታህሳስ 02/2018
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በGIZ ከሚደገፈው እና Light for the world ከተሰኘ ፕሮጀክት ጋር በመተባበር በቡናው ዘርፍ ለተሰማሩ አካል ጉዳተኞች ትኩረት መስጠት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በአዳማ ከተማ ስልጠና በመስጠት ላይ ነው፡፡ ስልጠናውን በመስጠት ላይ የሚገኙት Light for the world ፕሮጀክት በተለያየ የሀላፊነት ደረጃ ላይ የሚገኙ እና የካበተ ልምድ ያላቸው አካል ጉዳተኛ ባለሙያዎች ሲሆኑ ሰልጣኞች ደግሞ በባለስልጣን መ/ቤቱ ባለሙያዎች እንዲሁም ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ናቸው፡፡
የፕሮጀክቱ አስተባባሪ የሆኑት አቶ መላኩ በስልጠናው መክፈቻ ላይ እንዳሉት አካል ጉዳተኞች ለሀገር ግንባታ ያላቸው አበርክቶ ከፍተኛ መኾኑን፤ ሆኖም በህብረተሰቡ ዘንድ ባለው አመለካከት በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና በፖለቲካዊ ዘርፎች ላይ በሚጠበቀው ልክ ተጠቃሚ አለመሆናቸውን የጠቆሙ ሲሆን በይበልጥ አመለካከት መገንባት ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በፕሮጀክቱ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ዶ∕ር ዮሀንስ ለስልጠና ባቀረቡት ሰነድ በቡናው ዘርፍ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ ውስንነትን በማስተካከል የጋራ ተጠቃሚነትን ማጉላት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። የቡና ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች እንደልባቸው ተንቀሳቅሰው ለመስራት፤ ቡናቸውን ለመንከባከብ፣ ለመልቀም ያለው ግብግብና እልህ አስጨራሽ ጉዞ በተመለከተ ቀደም ሲል በተዘጋጀ ስልጠና ተገኝተው ተሞክሯቸውን ያካፈሉት በጅማ አጋሮ ነዋሪ የሆኑ አቶ መሀመድን እንደ አብነት በመጥቀስ አስረድተዋል∶∶ አቶ መሀመድ ቀደም ሲል እንዳሉት አመቺ መንገድ ስላልተዘጋጀና ቡናቸውን ወደገበያ ለመውሰድ ያለው የመሰረተ ልማቴ አመቺ ባለመሆኑ ሌሎች ጎረቤቶቻቸው ከሚሸጡበት በእጅጉ ባነሰ ዋጋ ምርታቸውን ለመሸጥ መገደዳቸው የሌሎች አካል ጉዳተኞችም የህይወት ገፅ መሆኑን እና አገልግሎት ፍለጋ ወደተለያዩ ቢሮዎች ሲሄዱም የሚገጥማቸው ከዚህ ብዙም ያልራቀ መሆኑንም አብራርተዋል∶∶
አማካሪው እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች የአገልግሎቱ ፍትሃዊ ተጠቃሚዎች ለማድረግ አገልግሎት ሰጪ ተቋማቱ የምልክት ቋንቋ ባለሙያዎች እንደሚያፈልጋቸው፣ የስራ ማስታወቂያዎችም ቢሆኑ አካል ጉዳተኞችን ጭምር ታሳቢ ያደረጉ መሆን እንዳለባቸው፣ ዓይነ ስውራን ደግሞ በብሬል እየታገዙ መረጃው የሚያገኙበት አማራጭ ሊፈጠር እንደሚገባም ጠቅሰዋል። መልካም ጅምሮች እንዳሉ የገለጹት ዶ∕ር ዮሀንስ ከችግሩ ስፋት አንፃር በተለየ ትኩረት እንዲሰራበትም አሳስበዋል።
በመሆኑም ያሉ ችግሮች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ቀዳሚው ተግባር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መሆን ያለበት ሲሆን የህብረተሰቡ ግንዛቤ ካደገ ችግሮቹን የመፍታት ጉዳይም የራሱ የህብረተሰቡ ይሆናል ብለዋል ።
ሀብታሙ መብራቱ በቦታው ተገኝቶ ዘግቦታል∶∶
