በ2018 በጀት ዓመት በ10 ወራት ከወጪ ንግድ 8.71 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኘ።
****
(ግንቦት 06 ቀን 2018 ዓ.ም አዲስአበባ ) በ2018 በጀት ዓመት የ10 ወራት የወጪ ንግድ አፈጻጸም ከታቀደው ግብ በላይ እጅግ አበረታች ውጤት መመዝገቡን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ካሳሁን ጎፌ ገለጹ።
ክቡሩ ሚኒስትሩ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ 10 ወራት ውስጥ 7.25 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ፣ 8.71 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በማስመዝገብ የዕቅዱን 120.17 በመቶ ማሳካት ተችሏል። ይህ አፈጻጸም ባለፈው ዓመት (2017 ዓ.ም) ተመሳሳይ ወቅት ከተመዘገበው የ6.08 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ጋር ሲነጻጸር የ43.32 በመቶ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱንም አብራርተዋል።
ይህ ስኬት በዋናነት በንግድ ዘርፉ ላይ የተወሰዱ የፖሊሲ እርምጃዎች ውጤት መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቁመው፤ በላኪዎችና በዘርፉ ተዋንያን መካከል የተፈጠረው ጥንካሬ እንዲሁም የልማት አጋሮች ጥረት የታከለበት መሆኑን አመልክተዋል።
በወጪ ንግድ ዘርፍ እየተመዘገበ ያለው ተከታታይ ስኬት የሪፎርም ሥራዎች ፍሬ እያፈሩ መሆኑን የሚያሳይ ትልቅ ማሳያ መሆኑን የገለጹት ክቡር ዶ/ር ካሳሁን፤ በቀሪዎቹ ወራትም ይህንኑ የላቀ አፈጻጸም በማስቀጠል ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ሽግግሩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።






