Standard Storage and Handling for Quality and Competitiveness!
Back

Standard Storage and Handling for Quality and Competitiveness!

ECTA
5 min read

"ደረጃውን የጠበቀ ማከማቻና አከመቻቸት፣ ለጥራትና ለብቁ ተወዳዳሪነት!"

የዚህ አጭር ጽሁፍ ዋና ዓላማ በቡና ግብይት ሰንሰለት ውስጥ የሚሳተፉ አርሶ አደሮች፣ አዘጋጆችና ላኪዎች በቡና ምርት አከመቻቸትና ጥራት አጠባበቅ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ ኖሯቸው በሃገር ውስጥም ሆነ በዓለም ገበያ ብቁ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማስቻል ነው።

1. በአርሶ አደር ደረጃ የቡና ምርት አከመቻቸትና ጥራት አጠባበቅ

አርሶ አደሩ የጀመሪያው የቡናው ባለቤት እንደመሆኑ ቡናን በአግባቡ ከመልቀም ጀምሮ በትክክል ማድረቅና ማከማቸት ለቡና ጥራት መሰረት ነው፡፡ የተለቀመውን ቀይ እሸት ቡና በአውድማ ወይም በአልጋ ላይ በማድረቅ የእርጥበት መጠኑ ከ10.5-12% እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል።

የማከማቻና ሁኔታና አከመቻቸት፡-

• ግድግዳውና ጣሪያው ከቆርቆሮና ወለሉ በስሚንቶ የተሠራ በቂ ስፋት ያለው፤

• ዝናብና ጎርፍ የማያስገባ፣ ከቤት እንስሳት፣ ከጭስና ሽታ ካላቸው ነገሮች ንክኪ የራቀ፤

• ድርቀቱን ስለመጨረሱ ቡናውን በመቀሸር በእርጥበት መለኪያ መሣሪያ ማረጋገጥ፤

• በንፁህ ጆንያ አድርጎ ከግድግዳ፣ ከወለልና ጣሪያ እንዳይነካካ አድርጎ መደርደር፤

• በመጋዘን ውስጥ የሚቆይ ከሆነ በየጊዜው በመፈተሸ እርጥበቱ ከጨመረ አውጥቶ ማናፈስ፤

• ቡናው ሳይሸጥ የሚቆይ ከሆነ ቀሽሮ ከማቆየት ይልቅ በጀንፈልነቱ ማስቀመጥ ይመረጣል፤

• የቡና ምርት ቢኖርም ባይኖርም የቡናው መጋዘን ውስጥ ከቡና ውጪ ሌላ ማንኛውንም ነገር አለማስቀመጥ፡፡

በአከመቻቸት ሂደት ተገቢዉ ጥንቃቄ ካልተደረገ

ቡናው ከመሬት እርጥበትን በመሳብ ለሸጋታ (Mould) እና ለመጥፎ ሽታ ይጋለጣል፤ ተባይ ይፈጥራል፣ በመጨረሻም የቡናውን ጣዕም አፈር አፈር የሚል (Earthy) ወይም የሻገተ/ የተበላሸ (Musty) አላስፈላጊ ጣዕም ይፈጠራል። በዚህም ምርቱን የጥራት ደረጃው ይወርዳል፣ የሽያጭ ገቢው ይቀንሳል፣ አርሶ አደሩ ኑሮ እንዳይሻሻል ያደርጋል፡፡

2. በቡና ምርት ማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎች የመጋዘን አያያዝና አከመቻቸት

የቡና ምርት ማዘጋጃዎች (የመጀመሪያ ደረጃ የደረቅ ቡና ማበጠሪያዎች፣ የታጠበ ቡና መፈልፈያዎች እና የኤክስፖርት ቡና ማዘጋጃዎች) ከፍተኛ መጠን ያለው ምርት ስለሚይዙ ሳይንሳዊ የክምችት ዘዴን መከተል ወሳኝ ነው።

የማከማቻ መጋዘኖችና አከመቻቸት፡-

• ግድግዳዉ ከብሎኬት/ከቆርቆሮ ወለሉ ከስሚንቶ የተሠራ የግድግዳ የላይኛው ጫፍ ለአየር ማስገቢያ የወንፊት ሽቦ የተገጠመለት በቂ ስፋት ያለው ፤

• ጣሪያቸው ከወለል በጣም ከፍ ያለ እርጥበትን የማያስገባ መሆን አለበት፣

• ንፁህ፣ ቀዝቃዛ፣ ደረቅና አየር በደንብ የሚዘዋወርበት፤

• ከመጋዘኑ ግድግዳ ቢያንስ 30 ሣንቲ ሜትር አርቆና ከጣራው አንድ ሜትር ዝቅ አድርጎ መደርደር፣

• ከወለሉ 20 ሣንቲ ሜትር ከፍ ብሎ በተሰራ የእንጨት ወይም የፕላስቲክ ርብራብ (Pallets) ላይ መከማቸት ይኖርበታል።

• በድርድሮች መካከል ለመተላለፊያ 50 ሣንቲ ሜትር መተው፣

• "ቀድሞ የገባ ቀድሞ ማዉጣት" first in first out (FIFO) የሚለውን የክምችት መርህ በመከተል የምርት መበላሸትን መከላከል ይገባል።

• ቡናው ከተዘጋጀ በኋላ እርጥበት እንዳይስብ አየር በማያስገቡ ከረጢቶች (Hermetic bags) መጠቀም ይመከራል።

• የቡና ምርት ቢኖርም ባይኖርም የቡናው መጋዘን ውስጥ ከቡና ውጪ ሌላ ማንኛውንም ነገር አለማስቀመጥ፡፡

ተገቢዉ ጥንቃቄ ካልተደረገ ማለትም መጋዘኑ ውስጥ ከፍተኛ ሙቀትና እርጥበት ከተፈጠረ ቡናው "ኬሚካላዊ ለውጥ" (Oxidation) ስለሚያደርግ በተለይ የተቀሸረ ቡና ከሆነ ቀለሙ ወደ ነጭነት ይለወጣል (Bleached)፤ ይህም በዓለም ገበያ ተቀባይነትን ያሳጣዋል።

በኢንዱስትሪ ደረጃ የሚከሰት ብክነት ከፍተኛ የገንዘብ ኪሳራን ከማስከተሉም በላይ፣ ተቋሙ ከባለሥልጣኑ የሚሰጠውን የብቃት ማረጋገጫ እስከማጣትና የንግድ ሥራው እስከመዘጋት ሊያደርስ ይችላል።

3. በቡና ላኪዎች (Exporters) የቡና ምርት አያያዝና ጥራት አጠባበቅ

ለኤክስፖርት የሚዘጋጅ ቡና መጋዘንና አከመቻቸት

• ግድግዳዉ ከብሎኬት ወለሉ ከስሚንቶ የተሠራ የመጋዘኑ የግድግዳ ጫፍ ለአየር ማስገቢያ ወንፊት ሽቦ የተገጠመለት ወይም ዘመናዊ የአየር መሳቢያና ማስወጫ መሣሪያ የተገጠመለት በቂ መጋዘን ፤

• ንፁህ፣ ቀዝቃዛ፣ ደረቅና አየር በደንብ የሚዘዋወርበት መጋዘን መጠቀም፤

• መጋዘኑ ቡናውን ቀጥታ የፀሐይ ብርሃን የማያገኘው ተደርጎ መሰራት ይኖርበታል፤

• የመጋዘኑ የውስጥና ምዝን የአየር እርጥበት ከ60 በመቶ በላይ እንዳይሆን መከታተል፤

• የመጋዘኑ የሙቀት መጠን ከ20- 25 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ዝቅና ከፍ እንዳይል መቆጣጠር፤

• የእርጥበት፣ የሙቀት መጠንና የውሃ እንቅስቃሴ መለኪያዎች ማሟላት፤

• ለኤክስፖርት የተዘጋጀ የቡና ምርትን ለረጅም ጊዜ አለማከማቸት፤

• ለምግብ መያዣነት የተፈቀደ ንጹህ የቃጫ ጆንያ (Jute bag) እና የተፈቀዱ መያዣዎችን መጠቀም፣

• በኮንቴይነር ለሚጭኑ ከዝገትና ከእርጥበት የጸዳ መሆኑ ማረጋገጥ፤

• አየርንና እርጥበትን ሙሉ በሙሉ ዘግተው በመያዝ የቡናው መዓዛ ሳይጠፋና በነቀዝ ሳይጠቃ ለረጅም ጊዜ እንዲቆይ የሚያስችሉ ዘመናዊና ለአካባቢ ተስማሚ የሆኑ (Grain Pro and Eco-tact)" የፕላስቲክ ማሸጊያዎችን መጠቀም፤

• ከማሸጊያው ውስጥ አየርን ሙሉ በሙሉ በመምጠጥና አሽጎ በመያዝ ምርቱ ከኦክስጅንና ከእርጥበት ጋር እንዳይገናኝ በማድረግ መዓዛው፣ ጣዕሙ የመጠቀሚያ ጊዜው ለረጅም ጊዜ እንዲቆይ የሚያስችል ዘመናዊ "Vacuum Packaging" የማሸጊያዎችን መጠቀም፤

• ለኮንቴይር ጭነት የላይነር (Liner bag) አጠቃቀምን በአግባቡ መተግበር፤

• የቡና ምርት ቢኖርም ባይኖርም የቡናው መጋዘን ውስጥ ከቡና ውጪ ሌላ ማንኛውንም ነገር አለማስቀመጥ፡፡

4. የውሃ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር መደረግ ያለባቸው ጥንቃቄዎች

የውሃ እንቅስቃሴ (water activity) ማለት በቡና ፍሬ ውስጥ የሚገኝ ነጻ የሆነ የውሃ መጠንን የሚያመለክት ሆኖ የቡናውን የቆይታ ጊዜ የሚወስን ሁል ጊዜ ከ 0.1 እስከ 1.0% ያህል ነው፡፡ በ0.55 እና 0.60% መካከል ቡና የተፈጥሮ ባህሪውን ይዞ ለመቆየት ምቹ ሲሆን ከ0.60 በላይ ከሆነ ደግሞ የረቂቅ ተህዋስያን የመባዛትና የሻጋታና ፈንገስ የመፍጠር ዕድሉ ስለሚጨምር የቡናውን የቆይታ ጊዜ ያሳጥራል፡፡ ስለሆነም በቡና ውስጥ የሚኖረውን ነጻ የውሃ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር የቡናው የእርጥበት መጠን (ከ11.5-12%) እንዲይዝ ማድረግ፤ንፁህ፣ ቀዝቃዛ፣ ደረቅና አየር በደንብ በሚዘዋወርበት መጋዘን ውስጥ ማከማቸት፤ ደረጃውን የጠበቀና የተፈቀደ የቃጫ ጆንያ መጠቀም፤ የእርጥበት፣ የሙቀት መጠንና የውሃ እንቅስቃሴ /free water activity/ መለኪያዎች ማለትም ምዝን የአየር እርጥበት መጠን (Relative Humidity) መለኪያ እና ከባቢያዊ የሙቀት መጠን (thermometer) መለኪያዎችን በማሟላት መቆጣጠር ወሳኝ ነው፡፡

5. አጠቃላይ በአከመቻቸት ስህተት የሚያስከትለው ጥቅል ጉዳት

በቡና አከመቻቸት ስህተት የሚመጣው ጉዳት በሦስት ደረጃዎች ሊታይ ይችላል፡-

• በጥራት ደረጃ (Quality Impact)፡- የምርቱን የጥራት ደረጃ በመቀነስ የቡናው ተፈጥሯዊ መዓዛ (Aroma) እና ጣዕም (Flavor) ይጠፋል። ይህም ኢትዮጵያ በዓለም የምትታወቅበትን የልዩ ጣዕም ባለቤትነት ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል።

• በጤና ደረጃ (Health Impact)፡- ተገቢ ያልሆነ ክምችት "ኦክራቶክሲን ኤ" (Ochratoxin A) የተባለ መርዛማ ፈንገስ እንዲፈጠር በማድረግ ለሰው ልጅ ጤና ጠንቅ ይሆናል በተጨማሪም በዓለም አቀፍ የጤና መስፈርት መሰረት በዓለም ገበያ ምርቱ ውድቅ እንዲሆንና ተፈላጊነት እንዲያጣ ያደርጋል።

• በኢኮኖሚ ደረጃ (Economic Impact)፡- በየዓመቱ በአያያዝ ጉድለት ምክንያት የሚባክነው ቡና ከጠቅላላው ምርት እስከ 10% ሊደርስ ይችላል። ይህ ማለት በሚሊዮን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሬ ሀገሪቱ ታጣለች ማለት ነው።

በአጠቃላይ የቡና ጥራት የሚጠበቀው ከቡና ማሳ እስከ ውጭ ገበያ ባለው ሰንሰለት ውስጥ ተገቢውን የክምችት ሥርዓት በጥብቅ በመከተል ሲሆን እርጥበትን መቆጣጠር፣ ከባዕድ ነገሮች መጠበቅ፣ ንጽህናን መጠበቅና በቂ የአየር ያለበት፣ ቀጥታ የፀሐይ ብርሃን የማያስገባ ቦታ ማከማቸት የቡናችንን ጣዕም፣ መዓዛና የሀገራችንን ገቢ የሚያረጋግጡ መሠረታዊ ተግባራት ናቸው። ቡናን በአግባቡ ማከማቸት ማለት ሀብትን መጠበቅ ማለት ሲሆን አርሶ አደሩ፣ ምርት ማዘጋጃዎችና ላኪው በቅንጅት የክምችት ምክረ-ሃሳቦችን ሲተገብሩ የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ገበያ ተፈላጊ እና ተመራጭ ሆኖ ይቀጥላል። ጥራትን መጠበቅ የአንድ ወገን ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን ቅንጅትንና መናበብን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው።

በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን

የቡና ሻይና ቅመማቅመም ምርት ዝግጅት መሪ ሥራ አስፈጻሚ

Gallery

Gallery image 1
Gallery image 2
Gallery image 3

Tags

#ECTA#coffee