የተሰጠው ስልጠና የንግድ ስምምነቶችንና አማራጭ የውጭ የገበያ እድሎችን እንድናውቅና እድሎችን እንድንጠቀም ያስችለናል። ተሳታፊዎች
አዲስ አበባ: መጋቢት 4/2018 ዓ.ም የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከትሬድ ማርክ አፍሪካ (Trade Mark Africa) ጋር በመተባበር በንግድ ህጎች፣ በንግድ ስምምነቶችና በአማራጭ የወጭ ንግድ የገበያ እድሎች ዙሪያ በወጪ ንግድ ለተሰማሩ ሴት ነጋዴዎች በቢሾፍቱ ከተማ ሲሰጥ የነበረውን ስልጠና አጠናቋል።
የስልጠናው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የንግድ ህጎችን፣ የተደረጉ የንግድ ስምምነቶችንና አማራጭ የወጭ የገበያ እድሎችን እንዲሁም አስቻይ ሁኔታዎችንና እንቅፋቶችንም እንድናውቅና በእውቀት ላይ ተመስርተን ንግዳችንን እንድንሰራ ያስችለናል ብለዋል።
ከኢትዮጵያ ጋር የንግድ ስምምነት የፈረሙ ሀገራትን፣ የአንድ ወገን የገበያ እድል የሰጡ ሀገራትንና ሌሎች ምርቶቻችንን የመግዛት አቅም ያላቸውን ሀገራት እንድንለይና ከነዚህ ሀገራት ጋር የንግድ ትስስር በመፍጠር የገበያ እድሎችን በመጠቀም የውጭ ንግዳችንን እንድናሳድግ ትልቅ አቅም ይፈጥርልናልም ብለዋል።
የስልጠና መድረኩን ያመቻቸው በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ስራ አስፈፃሚ ከትሬድ ማርክ አፍሪካ ጋር በመተባበር ሲሆን ስለ መሪነትና ስርዓተ ፆታን አስመልክቶም ስልጠና ተሰጥቷል።









