ጥቅምት 11/2018
አዲስ አበባ
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ቡና አምራች ለሆኑ አምስት ክልሎች በዛሬው እለት የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዙ 100 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው የመረጃ መሰብሰቢያ ዘመናዊ ስልኮችንና ለቡና ጉንደላ የሚያገለግሉ ግብአቶችን አስረክቧል።
የተከፋፈሉት እነዚህ ስማርት ሞባይል ቀፎዎች የአውሮፓ ህብረት በቅርቡ ተግባራዊ የሚያደርገው EUDR መመሪያ ጋር ተያይዞ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን በጠበቀ ሁኔታ የተሟሉ መረጃዎችን ለማሰባሰብ እና የቡና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የላቀ አስተዋጽኦ ሊኖራቸው እንደሚችል በማመን መሆኑን የባለሥልጣን መ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር አዱኛ ደበላ ተናግረዋል።
ከGIZ እና UNIDO ጋር በመተባበር ዱካውን የተከተለ የቡና ምርት ለአውሮፓ ህብረት ለማቅረብ የሚያስችል ሲስተም ዘርግተናል ያሉት ክቡር ዋና ዳይሬክተሩ በባለፈው ሳምንት ሀዋሳ ላይ አ/አደር ማሳ ላይ ሙከራ /Validate የማድረግ ስራ መሰራቱን እና በቅርቡ አ/አበባ ላይ የመጨረሻ ሙከራ ከተደረገ በኋላ መመሪያውን ለመተግበር የሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚደረስ ጠቁመዋል።
ወደ አውሮፓ ሀገራት ቡና ለመላክ የተቀመጡትን መስፈርቶች በተመለከተ ለባለድርሻ አካላት ተከታታይ የግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ሲከናወን መቆየቱንም አስረድተዋል።
ክልሎችም እነዚህን የተከፋፈሉ ስማርት ስልኮች ለታለመው አላማ ውለው አስፈላጊ መረጃዎች ሁሉ በትክክል ሊሰበሰቡ ይገባል ካሉ በኋላ ይህን ስራ እዚህ ደረጃ እንዲደርስ አስተዋጽኦ ለነበራቸው GIZ፣ UNIDO፣ UNDP እንዲሁም ክልሎች የላቀ ምስጋና አቅርበዋል።
የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታጋይ ኑሩ በበኩላቸው መረጃ የማደራጀት ስራ የቡና አመራረት ከደን ምንጣሮ በጸዳ መልኩ ለመከናወኑ ማረጋገጫ ከማቅረብ ባለፈ ከቡና ጋር የተያያዙ መረጃዎችን የማደራጀት አቅም ይፈጥራል ብለዋል።
መረጃዎቹ በቡና ምርታማነት ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በመለየት ለችግሮች አፋጣኝ መፍትሄ ለመስጠት እንደሚያስችሉም ጠቅሰዋል።
የየክልሉ ተወካዮች ስጦታዎቹን ከተረከቡ በኋላ ለተደረገው ድጋፍ ልባዊ ምስጋና አቅርበው የተረከቡትን የግብርና ግብዓት ስልጠና ለወሰዱት አካላት እንደሚያስረክቡና ለታለመለት አላማ እንደሚውልም ጨምረው ገልጸዋል።






