ኢትዮጵያና ኮሎምቢያ የሁለትዮሽ የንግድ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ።
(አዲስ አበባ : መጋቢት 29 ቀን 2018 ዓ.ም) የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ክቡር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የኮሎምቢያ አምባሳደርና በአፍሪካ ሕብረት የኮሎምቢያ ቋሚ መልዕተኛ ከሆኑት ክቡር የይሰን አርካዲዮ ሜኔሴስ ኮፔቴ ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ተወያይተዋል ።
በውይይቱም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር በሚቻልባቸውና በጋራ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ምክክር ተደርጓል ።
ክቡር ሚኒስትሩ በንግግራቸው ወቅት ኢትዮጵያና ኮሎምቢያ እ.ኤ.አ ከ1949 ጀምሮ የቆየ ታሪካዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን አስታውሰው፣ በአዲስ አበባ የኮሎምቢያ ኤምባሲ ዳግም መከፈቱ ግንኙነቱን ይበልጥ ለማጥናት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል ።
በተለይም ኢትዮጵያ የጀመረችውን የማክሮ-ኢኮኖሚ ሪፎርምና ወደ ዓለም የንግድ ድርጅት (WTO) ለመግባት የምታደርገውን ጥረት በማብራራት፣ በዚህ ረገድ የኮሎምቢያ ድጋፍና ተሞክሮ ለኢትዮጵያ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል ።
የሁለቱን ሀገራት የንግድ ልውውጥ ባለፉት አምስት ዓመታት መሻሻል እያሳየ ቢሆንም አሁንም ያልተነኩ በርካታ ዕድሎች መኖራቸውን ሚኒስትሩ አብራርተዋል ።
ባለፉት ዓመታት የሁለቱ ሀገራት የንግድ ልውውጥ በአማካይ ሁለት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር አካባቢ የነበረ ሲሆን፣ ይህንን ቁጥር ለማሳደግ ሁለተኛውን የሁለትዮሽ የንግድ ውይይት ማካሄድና ቀደም ሲል የተጀመረውን የንግድ የጋራ መግባቢያ ሰነድ (MoU) ማጠናቀቅ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መግባባት ላይ ተደርሷል ።
በመጨረሻም ክቡር ዶ/ር ካሳሁን ኢትዮጵያ ኮሎምቢያን እንደ የንግድ አጋር ብቻ ሳይሆን እንደ የልማት አጋር እንደምትመለከታት ገልጸው፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሁለቱን ሀገራት የንግድ ግንኙነት ለማጠናከርና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል ።
አምባሳደር የይሰን አርካዲዮ በበኩላቸው ኮሎምቢያ ከኢትዮጵያ ጋር በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች በቅርበት ለመሥራት ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል ።







